አፈናው ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ አትገባም ከሚል ለሕክምና ከኢትዮጵያ አትወጣም ወደሚል ተዛምቷል ! = ክርስቲያን ታደለ

ሕክምና መከልከል ከመግደል እኩል ነው!

በሕመም ላይ የሚገኙትን ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በቤታቸው ተገኝተን ጠይቀናቸዋል። ስለጤናቸው እና የሕክምና ፍላጎታቸውም ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ጄኔራል መኮንኑ ሕክምና የጠየቃቸው የእግር ሕመም ለአገራቸውና ለሕዝባች ሲሉ ሲታገሉ በጥይት በመመታታቸው ነው።

ለአገር እና ሕዝብ የተዋጉት ጄኔራል ደማቸውን ያፈሰሱት ለግል ፍላጎታቸው ሲባዝኑ አልነበረም። እንደወጉ ቢሆን የአገር መከላከያ ሰራዊት የእኒህን ጄኔራል መኮንን የሕክምና ወጪ በመሸፈን ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲያገኙ ማስቻልን ጨምሮ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ መፈፀም ነበረበት።

«ጽድቁ ቀርቶ በቅጡም በኮነነኝ» እንዲሉ በደጋጎች ቸር አድራጎት ታግዘው ሕክምና ለማድረግ ወደ እስራኤል ለመብረር ቢወጥኑም የኤርፖርት የፀጥታ ኃላፊዎች «የበላይ አካል ትእዛዝ» ነው በሚል ፓስፖርታቸውን ቀምተው «ቀርቷል» የሚል ቃል በእስክርቢቶ ጽፈውበት ጉዞ ከልክለዋቸዋል።

አፈናው ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ አትገባም ከሚል ለሕክምና ከኢትዮጵያ አትወጣም ወደሚል ተዛምቷል። አትወጣም ማለት አትታከምም ማለት ነው። አትታከምም ማለት ደግሞ እንድትሞት እንፈልጋለን ማለት ነው። አፈናው ከዚህ ደርሷል።

መላው ኢትዮጵያውያን መንግስት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ሕክምና በመከልከል በሕይወታቸው ላይ አደጋ እንዲወድቅ የሚያደርገውን አፈና እንዲያወግዙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለጄኔራል መኮንኑም ፈጣሪ ምሕረትን እንዲያመጣላቸው በጎውን ሁሉ እንመኛለን።

ክርስቲያን ታደለ