በኢንዱስትሪ ፖርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ደመወዛቸው አነስተኛ በመሆኑ ወደ ወሲብ ንግድ ተሰማርተዋል

” በኢንዱስትሪ ፖርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ደመወዛቸው አነስተኛ በመሆኑ ወደ ወሲብ ንግድ ተሰማርተዋል ” የጨርቃጨርቅ ፌዴሬሽን

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ ኑሮን ለማሸነፍ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ወደ ወሲብ ንግድ እየተሰማሩ መሆኑ የጨርቃጨርቅ ፌዴሬሽን ገልጿል።

የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተወካይ የሆኑት አቶ ተስፋዬ አብዲሳ ሰራተኞቹ ከወሲብ ንግድ በተጨማሪ ትርፍራፊ ምግቦችን ከየሆቴሉ በመሰብብ ወደ ቤታቸው የሚወስዱ መኖራቸውን ተናግረዋል።

አምራች ስራተኛ፣ ምቹ ስራ ለወጣቶች እና ሴቶች በጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ መፍጠር በሚል ርዕስ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቋማዊ ጥናት ለማድረግ የማህበራት ጥናት መድረክ (Forum For Social Studies) ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱ ላይ የተገኙት የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ተስፋዬ አብዲሳ ” በሰራተኞች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት አረጋግጠናል ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ስራተኞች ገቢያቸው እንዲሻሻል ለማድረግ  ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ማፅደቅ አንዱ መፍትሄ ነው ያሉት ተወካዩ ‘’በተለይ ለሴቶች ክፍያው ዝቅተኛ ስለሆነ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት አረጋግጠናል ነው ያሉት።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ አሰሪዎች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ፈቃደኞች እንዲሆኑ ቢያረጋግጢም በመንግስት በኩል ግን እግሩን የሚጎትትበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አካላት በኢንዲስትሪ ፓርኮች በጨርቃ ጨርቅ እና ጋርመንት ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ ትዳር የሚመሰርቱት ስለፈለጉ ሳይሆን ወጪ ለመጋራት እንደሆነ እና በትዳር ሕይወታቸው ላይ እንኳን የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው አድርጓል ነው ያሉት።

ተወካዩ አቶ ዘሪሁን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ወርሃዊ ክፍያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲተያይ እጅግ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

የዚህ የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ዶክተር ደግነት አበባው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ አስፈላጊነቱ የማየጠራጥር መሆኑን ገልፀው ነገር ግን እንዴት ይወሰን የሚለውን በደንብ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ነገ ሀሙስ በአለም አቀፍ የሚከበረውን የሰራተኞች ቀንን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የዝቀተኛ ደመወዝ ወለል እንዲወስን የጠየቀው ጥያቄ መልስ እንዳላገኘለት አመላክቷል።

Source : ShegerFM102.1