በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የመጥፋት አደጋ በተጋረጠበት ብርቅዬው ዋሊያ አይቤክስ ላይ በግንቦት ወር ቆጠራ እንደሚደረግ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማሩ ቢያድግልኝ ለዋዜማ ተናግረዋል። የዋሊያ ቁጥር መመናመን የጀመረው፣ ከፓርኩ ገቢ የሚያገኙ የፓርኩ አጋዥ ጠባቂ ሚሊሻዊች በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሥራ ማቆማቸውን ተከትሎ ዋሊያ ለአደን በመጋለጡ እንደነበር የጠቀሱት ማሩ፣ የሰሜኑ ጦርነትም ለቁጥሩ መቀነስ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። በ2015 እና በ2016 ዓ፣ም በተደረገ ቆጠራ፣ የዋሊያ ቁጥር ከ865 ወደ 306 ወርዶ መገኘቱን ዋዜማ ተረድታለች። በእርጥብና በደረቅ ወቅት በሚል በሁለት ዙር ቆጠራ የሚካሄድ ሲኾን፣ የግንቦቱ የእርጥብ ወቅት ቆጠራ ነው። በዓመት በአማካይ 30 ሺሕ የነበረው የፓርኩ ጎብኝዎች ቁጥር፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 3 ሺሕ ማሽቆልቆሉን ዋዜማ ተረድታለች።