
የፎቶው ባለመብት, sm
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ዮናታን ዳኛው እንዲሁም ሦስት የአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል ዶክተሮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአማራ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በቀናት ልዩነት የታሰሩ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር አምስት ደርሷል። በአዲስ አበባ ከተማ ሌሎች አምስት የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ከሁለት ቀን እስር በኋላ ተለቅቀዋል።
የጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ ድጋፉን የገለጸው የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ዮናታን የታሰሩት ትናንት እሁድ ግንቦት 3/2017 ዓ.ም. እንደሆነ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መለስ ባታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም. የተመሠረተውን ማኅበር የሚመሩት አቶ ዮናታን፤ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚገኘው ቢቸና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ መሆናቸውን አቶ መለሰ ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንደሚናገሩት አቶ ዮናታን እሁድ ከሰዓት የተያዙት ከመኖሪያ ቤታቸው ነው። “ከመያዙ በፊት ከትናንት ወዲያ [ቅዳሜ] የሚሠራበት ሆስፒታል አካባቢ እና በሚኖርበት ሰፈር [በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ] ለምርመራ እንደሚፈለግ ደውለው እንዳስታወቁት ነግሮኝ ነበር” የሚሉት አቶ መለስ፤ ይህ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ከማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጋር አጭር የስልክ ንግግር ማድረጋቸውን የሚጠቅሱት አቶ መለስ፤ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኝ እና “ብዙ ችግር እንዳልደረሰበበት” ከራሱ መስማታቸውን ገልጸዋል። ይሁንና የስልክ ጥሪው በመቋረጡ ምክንያት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የታሰሩበትን ምክንያትም ሆነ ስለተደረገባቸው ምርመራ በዝርዝር መነጋገር እንዳልቻሉ አክለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ መለሰ ግን የአቶ ዮናታን እስር “የጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አቶ መለሰ ለዚህ እምነታቸው በማሳያነት የሚጠቅሱት ለማኅበሩ ፕሬዝዳንት እና በራሳቸው ላይም ጭምር ይደርስ ነበር ያሉትን “ማስጠንቀቂያ” ነው።
ማኅበሩ በጤና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች “በአግባቡ እንዲመለሱ” የሚያሳስብ ደብዳቤዎችን መጻፉን የሚያስታውሱት አቶ መለስ፤ “[እስሩ] ከማኅበሩ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው ብለው በደንብ ነው የምናምነው። ምናልባት የያዘው አካል ከሌላ ጋር ሊያያይዘው ይችላል እርሱ እኛን የሚመለከት አይደለም” ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች ለዓመታት ሲያነሷቸው የነበሩ የደመወዝ እና ሌሎች ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ አድማ እንደሚመቱ ከሰጡት ማስጠንቀቂያ ጋር “በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት” አቶ ዮናታን ብቻ አይደሉም። ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 1/2017 ዓ.ም. ሦስት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ዶክተሮች በፖሊስ እንደተያዙ የቤተሰብ አባሎቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር በርናባስ ሳሙኤል፣ ዶ/ር መላኩ አልማው እና ዶ/ር ሀብታሙ ጌታቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ዶክተሮች ናቸው። የጤና ባለሙያዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ አርብ ዕለት የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴን በመደግ በሕብረት የተነሱት ፎቶ ግራፍ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋሩ በኋላ እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
አንድ የቤተሰብ አባል፤ “ይህንን ተከትሎ ከሰዓት ላይ የአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊዎች ሦስቱን ዶክተሮች ወደ ሆስፒታል እንዲመጡ ጠሯቸው” ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ በሆስፒታሉ ሲደርሱ አካባቢው ላይ “የመንግሥት ኃላፊዎች እና የፀጥታ ኃይሎች” ተገኝተው እንደነበረም ገልጸዋል። ሦስቱ ዶክተሮች “የጤና ባለሙያዎችን እንቅስቃሴ በማስተባበር” ተጠርጥረው በጋሞ ዞን ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩም አክለዋል።
ከጤና ባለሙያዎች ጋር “መነጋገራቸው እና ስምምነት ላይ መድረሳቸውን” ለቢቢሲ የተናገሩት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አምባቸው ዱማ፤ የሦስቱን ዶክተሮች እስር አስተባብለዋል። ሥራ አስኪያጁ፤ “የታሰረ ሰው የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አራት የጤና ባለሙያዎችም በተመሳሳይ በጤና ተቋሙ ውስጥ ተሰብስበው ለእንቅስቃሴው ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹ በኋላ ታስረው ነበር። በንፋስ ስልክ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጤና ጣቢያ ሠራተኛ የሆኑ አራቱ የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም. ነበር።
ታስረው ከነበሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል ለ30 ዓመታት ያገለገሉት የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዋ ደግነሽ ጥላሁን ይገኙበታል። የጤና ባለሙያዋ ባለቤት ቄስ ዳዊት ጋሩማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዕለቱ የጤና ባለሙያዎች ተሰብስበው ለእንቅስቃሴው ያላቸው ድጋፍ ገልጸው ነበር።
ከዚህ በኋላ ከሰዓት ላይ የፖሊስ አባላት የጤና ባለሙያዎቹ ከሚሠሩበት ጤና ጣቢያ ወስደው ጀሞ ሚካኤል አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዳሰሯቸው የሁለት ጤና ባለሙያዎች የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ አርብ ግንቦት 1/2017 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በመታወቂያ ዋስ መለቀቃቸውንም ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
አራቱ የጤና ባለሙያዎች በተለቀቁበት አርብ ዕለት ደግሞ የፋርማሲ ባለሙያ የሆነው ገብሩ መላክ በቁጥጥር ስር ውሏል። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ጤና ጣቢያ ሠራተኛ የሆነው ገብሩ የተያዘው ከሥራ እየወጣ ባለበት ሰዓት እንደሆነ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የቅርብ ጓደኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በአሁኑ ሰዓትም በመርካቶ አካባቢ በሚገኘው አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደሚገኝ ምንጩ ገልጿል። የፋርማሲ ባለሙያው ገብሩ የታሰረው እንደ ሌሎቹ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ የጤና ባለሙያዎቹን እንቅስቃሴውን የሚደግፍ የቡድን ፎቶ ከተነሳ በኋላ ነው ተብሏል።
አርብ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለው ገብሩ፤ በማግስቱ ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት መቅረቡን የቅርብ ጓደኛው ተናግሯል። መርማሪ ፖሊስ በገብሩ ላይ እንዲፈቀድለት ከጠየቀው 12 የምርመራ ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤቱ፤ አምስት ቀናት እንደፈቀደም ገልጿል።
ገብሩ ከመታሰሩ አስቀድሞ በዚያው ጤና ጣቢያ ውስጥ አዋላጅ ነርስ የሆነው ሚካኤል ፀጋዬ ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። አዋላጅ ነርሱ ሚካኤል ከሁለት ቀናት እስር በኋላ አርብ ዕለት ተለቅቋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን አጋሮ ሆስፒታል ዶክተሮች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መፈታታቸው ተነግሯል።