ዮናስ አማረ
Reporter Amharic
ለ20 ዓመታት በተለያዩ የኅትመትና የዲጂታል መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ሲሠራ የቆየው ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት 11 ሰዓት ግድም የፌዴራል ፖሊስ የተካተተበት የፀጥታ ኃይሎች ወደ መኖሪያ ቤቱ እንደመጡ ይናገራል፡፡ እርሱም፣ ባለቤቱም ሆነ ልጆቹ በር ሲንኳኳ በሌሊት ‹‹የማን መርዶ ነጋሪ መጣ›› ብለው ተደናግጠው ከእንቅልፋቸው መንቃታቸውንም ይገልጻል፡፡ በሩን ሲከፍትላቸው ወደ ቤቱ የዘለቁት የፀጥታ ኃይሎች እንደሚፈለግና ይዘውት እንደሚሄዱ ነግረው፣ የእጅ ስልኩን ተቀብለው መታወቂያውን እንዲይዝ በማስታወስ አካልበው እንደወሰዱት ያስረዳል፡፡
‹‹ከሁሉ በላይ በልጆቼ ፊት ይህ መደረጉ ያሳዝነኛል፡፡ በአንድ መጥሪያ ና ቢሉኝ ካልፈለጉም በአንድ የስልክ ጥሪ ቢጠሩኝ የፈለጉበት ቦታ መገኘት የምችል ሰው ነበርኩ፤›› ሲል ስሜቱን ይገልጻል፡፡ ተደናግጠው ከእንቅልፍ የተነሱት ልጆቹ እሱ ሲወሰድ እያለቀሱ እንደነበር በመጥቀስ፣ ወደ መኪና ሲያስገቡትም በመስኮት እየተመለከቱ ሲያለቅሱ መመልከቱን ነው የተናገረው፡፡
በቀጥታ ሜክሲኮ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማቆያ እንደወሰዱት የተናገረው ጋዜጠኛ ፋኑኤል፣ በመጨረሻ ግን በስም ማጥፋት ወንጀል መከሰሱን እንደነገሩት ይገልጻል፡፡ ‹‹ታዘን ነው፣ እኛ የምናውቀው የለም፣ ወንጀሉ ከባድ ነው እያሉ ሲመልሱልኝ ቆይተው በመጨረሻ ግን የአንድ ግለሰብ ስም ጠርተው ስሜን አጥፍቷል የሚል ክስ እንደመሠረቱብኝ ነገሩኝ፡፡ አሁን በምሠራበት ፈንታሌ ሚዲያ በተባለ የራሴ የዩቲዩብ ሚዲያ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት በፊት በተላለፈ ዝግጅት የተነሳ በስም ማጥፋት መከሰሴንም ነው የነገሩኝ፤›› ሲልም ያስረዳል፡፡

ጉዳዩ በአዲስ አበባ ፖሊስ ለምን አይታይም ብሎ መጠየቁን ጋዜጠኛው ይናገራል፡፡ እንዲሁም ዋስትና ከማያስከለክሉ ከሁለት እስከ ስድስት ወር ከሚያስቀጡ ቀለል ያሉ ጥፋቶች አንዱ መሆኑን በመጥቀስ በዋስ እንዲወጣ መጠየቁንም ያክላል፡፡ ጉዳዩ በወንጀል የሚታይ ሳይሆን የፕሬስ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞችን ጉዳይ በሚመረምር ቦርድ አማካይነት የሚታይ ነው መሆን ያለበት የሚል ጥያቄ ማንሳቱንም ይገልጻል፡፡ ከሁሉ በላይ ክሱ በግለሰብ የቀረበ አቤቱታ በመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ አይመለከተውም ብሎ መከራከሩንም ይገልጻል፡፡ ጉዳዩ የመንግሥት ክስ አለመሆኑን፣ የአገር ደኅንነት፣ የሕዝብ ጥቅም ወይም ግጭትና ከባድ የሕግ ጥሰትን የተመለከተ ባለመሆኑ በፌዴራል ፖሊስ ተይዞ የሚቀርብበት ሳይሆን ከከሳሹ ከራሳቸው ጋር በሚደረግ ክርክር የሚዳኝ መሆኑን በማስታወስ መሞገቱን ይናገራል፡፡
‹‹የትም የማልሄድና መረጃም የማላጠፋ ሰው መሆኔን ገልጬ ዋስ፣ እንዲፈቀድልኝ ተከራክሬያለሁ፡፡ ከዚያም በላይ ከተላለፈ ረዥም ጊዜ በሆነው ፕሮግራም ላይ ተመሥርቶ የስም ማጥፋት ክስ ማንም ሊመሠርት እንደማይችል ጠቅሼ ተከራክሬያለሁ፡፡ አዳምጠህ ወይም አንብበህ ትከሳለህ እንጂ ባለፈ ፕሮግራም ላይ ተመሥርተህ ስሜ ጠፋ ማለት አትችልም፡፡ በመጨረሻ አቤቱታዬ ስለተሰማ መሰለኝ ጥቂት ቀናት አሳድረው ለቀውኛል፤›› ሲል የገጠመውን ሁኔታ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡
ያም ቢሆን ግን ገና እስካሁን ሥራ አለመጀመሩንና ካደረበት ሥጋት አለመላቀቁን ነው ፋኑኤል የተናገረው፡፡ ከዚህ ቀደም በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ጦርነት በተቀሰቀሰ ወቅት ከሚሠራበት ከአውሎ ሚዲያ ከመላ ባልደረቦቹ ጋር በፖሊሶች ተይዘው ለ26 ቀን የት እንዳሉ ሳይታወቅ ታስረው መለቀቃቸውን ይናገራል፡፡ ከዚያ ወዲህም ቢሆን በአዋሽ እስር ቤት ለሦስት ወራት ታስሮ እንደነበርም ይጠቅሳል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን በኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳሩ የሚያስመካ ደረጃ ላይ የደረሰ እንዳልነበረ የሚናገረው ጋዜጠኛ ፋኑኤል፣ በዚያን ወቅትም ለሚዲያዎችና ለጋዜጠኞች ብዙ ዓይነት ፈተና እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹ያኔ እኔ የምሠራበት ሚዲያ ለምሳሌ ለሰባት ጊዜ ማዕከላዊ እየተጠራን ቃል እየተቀበሉ ሲለቁን አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንዴም አሳድረው ሲፈቱን ኖረናል፡፡ ይሁን እንጂ የአሁኑ ሁኔታ ምን ሊገጥምህ እንደሚችልም ሆነ ምን እንደሚደርስብህ አለማወቅህ የበለጠ እንድትሠጋ የሚያስገድድ ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡
በፖለቲካ ሴራ በተሞላ አገር ውስጥ ያለችዋን ቀጭን መስመር ተከትሎ ለመሥራትም ከባድ እንደሆነ የገለጸው ፋኑኤል፣ የቅርብ ሰሞኑ እስራት በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣበት እንደሚችል ነው ያወሳው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስና እስራት ለማስደንገጥና ሥጋት ውስጥ ለመክተት ተብሎ ሊደረግ እንደሚችል በመጥቀስ፣ ‹‹ጋዜጠኞች የመንግሥትን ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳያነሱ ለማሸማቀቅ ተብሎ ሊደረግ ይችላል፡፡ በግሌ ምን ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ ሽፋኑ ስም ማጥፋት የሚል ቢሆንም ነገር ግን እነማን እንደሆኑና ለምን እንዳደረጉት አልገባኝም፤›› ሲል ነው በግል የገጠመውን ታሪክ ያጋራው፡፡
ከፋኑኤል በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ሚያዚያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውሎ ከሁለት ቀናት እስራት በኋላ በዋስ የተፈታው የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ የጋዜጠኛ አበበ ፍቅር ጉዳይም ልክ እንደዚሁ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የተገኘው ቢሮ ድረስ መጥተው አቤቱታ ያቀረቡ ከመከላከያ የተሰናበቱ አካል ጉዳተኛ አባላትን ጉዳይ ከአስተዳደሩ አመራሮች ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት ነበር፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ስለጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሥራ ኃላፊዎች አስቀድሞ በስልክ አናግሮ የነበረ ሲሆን፣ በአካል መጥቶ መጠየቅ እንደሚችል ፈቃዳቸውን አግኝቶ ነበር ወደ ቢሮው ያመራው፡፡ በአስተዳደሩ ቢሮ ሲገኝም በዕለቱ ተሠልፈው አገልግሎት ሲጠይቁ ከነበሩ ባለጉዳዮች ጋር ተሠልፎ ለረዥም ሰዓታት ተራውን ሲጠብቅ ቆይቶ ነበር ወደ የሚመለከተው ኃላፊ ቢሮ የገባው፡፡
ከሥራ ኃላፊዎቹ ጋር ያደረገው ግንኙነት ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ‹‹መታወቂያ አምጣ፣ ፎቶ ለምን አነሳህ? ቪዲዮ ለምን ቀረፅክ›› ወደ የሚል የቃላት ልውውጥ አመራ፡፡ ጋዜጠኛው በአካል ከቅሬታ አቅራቢዎች የመጣ ቅሬታ ተቀብሎ ለማጣራትና ሚዛናዊ ዘገባ ለመሥራት ጥረት እያደረገ መሆኑን በተደጋጋሚ ጠቅሶ ቢያሳውቅም ነገር ግን፣ ‹‹ተልዕኮህ ምንድነው? ምን አስበህ ነው? ማን ነው የላከህ?›› የሚሉ አፀፋዎችንና ማጎሳቆል ብቻ ማግኘቱን ይገልጻል፡፡ ማዋከብ በተሞላበት ሁኔታ የተለያዩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ ተደርጎና ፖሊስ ተጠርቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደ ሲሆን ከሁለት ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ሲቀርብም ‹‹ጋዜጠኝነቱን የሚያመለክት ምንም ዓይነት መታወቂያ ሳይኖረው ክፍለ ከተማውንና ኃላፊዎቹን ቪዲዮ በመቅረፅና ፎቶ በማንሳት ሁከትና ረብሻ ለመፍጠር ሞክሯል›› የሚል ክስ ነበር የቀረበበት፡፡
ጋዜጠኛ አበበ ጉዳዩ ታይቶ በአሥር ሺሕ ብር ዋስ የተለቀቀ ቢሆንም፣ አጋጣሚው ግን ብዙ ጥያቄ አጫሪ ነበር፡፡ ለዚህ ጉዳይ መረጃ ማጣራት እፈልጋለሁ ብሎ አስቀድሞ ስልክ ደውሎ፣ እንዲሁም ከባለጉዳዮች እኩል ወረፋ ጠብቆ ኃላፊዎችን የሚያናግር ጋዜጠኛ በጥቂት አለመግባባትና በውኃ ቀጠነ ሰበብ ለእስር ሊዳረግ የሚችልበት ጊዜ እየተፈጠረ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ ጉዳዩ ያስነሳ ነበር፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ሹም በጋዜጠኞች ለሚጠየቀው ጥያቄ ቀና መልስ ከመስጠት ይልቅ ተልዕኮህ ምንድነው? እንዲያውም ዓይነ ውኃው አላማረኝም ብሎ የሥራ ባልደረቦችን ሰብስቦ ወደ ማዋከብና ማሳሰር መግባት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊስ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም እያጫረ ይገኛል፡፡ የቀዳው ድምፅ አለመኖሩን፣ ያነሳው ፎቶም ሆነ ቪዲዮ እንደሌለ ስልኩን ከፍቶ ለተሰበሰቡ ሰዎች በማሳየት አረጋግጦ ሳለ፣ እንዲሁም ፖሊሶቹ ጭምር በይቅርታ የሚታለፍ አለመግባባት መሆኑን እየገለጹ ባለበት ሁኔታ ፖሊስ ጣቢያ በማሳደርና ፍርድ ቤት በማቅረብ ጉዳዩን ማተለቅ ለምን ተፈለገ የሚለው ጉዳይም ሌላ ጥያቄ እያጫረ ነው፡፡
በቅርብ ወራት ከሚዲያና ከጋዜጠኝነት ጋር በተገናኘ ሌሎችም በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮች ተከስተዋል፡፡ ‹‹አዲስ ምዕራፍ›› በተባለው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የቀረበውና ከባድ ፖለቲካዊ ትኩሳት በአገሪቱ የፈጠረው ብርቱካን ተመስገን የተባለች ሴት ታሪክ ለጣቢያው ሰባት ሠራተኞች መታሰር መነሻ ሆኗል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የተደረገ የፖለቲካ ሴራ ነው ሲል የፈረጀው የብርቱካን ጉዳይ፣ ሰባቱ የጣቢያው ሠራተኞች በፀረ ሽብር አዋጁ እንዲከሰሱ ምክንያት ነበር፡፡ የሠራተኞቹ የፍርድ ሒደት ገና ያልተጠናቀቀና ጉዳዩም ገና የጠራ መልክ ያልያዘ ቢሆንም፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተከታታይ ዶክመንተሪዎችን በመሥራት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሲሰጡት ታይተዋል፡፡ የኢቢኤስን ታሪክ ተከትሎ ስለሚዲያዎች አሉታዊ ሚና ጎልቶ እንዲነገር በሰፊው መደረጉ፣ እንዲሁም ከሕግና ከፍርድ ሒደት ውጪ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሚዲያዎች በስም እየተጠቀሱ ይዘጉ፣ ይውደሙ የሚል ዘመቻ መካሄዱ የሚዲያ ምኅዳሩ ላይ ጥላውን ሊያጠላ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ቢሮ በፀጥታ ኃይሎች ሲወረር የድርጅቱ ሦስት ባልደረቦች ታሰሩ የሚለው የቅርብ ሰሞን ዜናም፣ እንዲሁ በኢትዮጵያ ስላለው የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ጥያቄ እንዲወረወር ያደረገ ሌላ ጉዳይ ነበር፡፡ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ፖሊስ ከአዲስ ስታንዳርድ ሦስት ባልደረቦች ጋር ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ዳታ ማከማቻ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ለምርመራ ይፈለጋሉ ብሎ መያዙን ድርጅቱ ያስታወቀ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ ያለ ክስ በአንድ ቀን ወዲያው መለቀቃቸውን ጠቅሶ ቁሳቁሶቹ ግን እንዳልተመለሱ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
እነዚህ ሁሉ በተቀራራቢ ጊዜ በአንድ ሰሞን የተፈጸሙ ሁነቶች የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ይዞታ ወዴት እያመራ ነው የሚል መሠረታዊ ጥያቄ እያስነሱ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አጋጣሚዎች ጎን ለጎን ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ መፅደቁ ደግሞ ስለዘርፉ ተደጋግሞ ጥያቄ እንዲነሳ እያደረገ ነው፡፡ የሚዲያ ዘርፍ ባለድርሻዎች በተለይም የግል ሚዲያዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሌሎች የሙያ ማኅበራት በማሻሻያ አዋጁ ላይ ጠንካራ ተቃውሞና ቅሬታ እያሰሙ ባሉበት በተቻኮለ ሁኔታ አዋጁ እንዲፀድቅ መደረጉ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ይዞታ ወደኋላ ሊመለስ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሮ ነው የሚገኘው፡፡
የነገሥታትን አዋዋልና ዕለታዊ የሥራ ክዋኔ በመዘከር የተዋወቀው የኅትመት ሚዲያ ቀጥሎ ለመጡት ለራዲዮና ለቴሌቪዥን ሚዲያዎችም መሠረት ነበር፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ተገዢነት ነፃ ባልወጡበት ወቅት ዘመናዊ ሚዲያን የተዋወቀችው ኢትዮጵያ ዛሬ ከሁለት የመንግሥት ጋዜጦች ውጪ ዕለታዊ ጋዜጦች የሌላት፣ ውስን ቁጥር ያላቸው የመንግሥት ብሮድካስተሮች ብቻ ባለቤት የሆነች ሆና ለምን እንደቀረች ሰፊ ምርምር ይጠይቃል፡፡ በየዘመናቱ ብልጭ ድርግም የሚል የምኅዳር መስፋት አጋጣሚዎችን ሲያይ የኖረው የኢትዮጵያ ሚዲያ ዘርፍ በተለይ ከኢሕአዴግ መንግሥት መምጣት ወዲህ ነው በሩ ወለል ብሎ ሲከፈትለት የታየው፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር የፕሬስ ነፃነት በሕግ የተደነገገውና በርካታ የግል ፕሬስ ውጤቶች የተበራከቱት፡፡
‹‹ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ›› የሚል መጽሐፍ በ2011 ዓ.ም. ያበረከቱት ለረዥም ዘመን በጸሐፊነት የሚታወቁትና አሁን በእስር ቤት የሚገኙት አቶ ታዴዎስ ታንቱ፣ ከኢሕአዴግ መምጣት ወዲህ 38 የግል ጋዜጦችና 52 መጽሔቶች በኢትዮጵያ መታተም ጀምረው እንደነበር በስምና በይዘት ጠቅሰው ከትበዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም 17 የስፖርት ጋዜጦችን ስምም አብረው ዘርዝረዋል፡፡ ‹‹የፕሬስ ሕጉ እንደወጣ ኅትመቶች እንደ አሸን ፈሉ፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ሙያዊ ብቃት አልነበራቸውም ነገር ግን ሰዎች ይገዟቸው ነበር፡፡ አገዛዙም የራሱን ጎራ ለይቶ እርሱን የሚያገለግሉትን አስፋፋ፡፡ በይዘቱ ሞቶ የተወለደው የሚዲያ ሙያ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ በሙያው በአንድ አገር ሁለት ጎራ ቆመ፡፡ መንግሥትን ያልደገፉ የግል ጋዜጦች እንደ አገዛዙ ባላንጣ መታየት ጀመሩ፤›› በማለት ነው አቶ ታዴዎስ የሙያውን አበቃቀልም በመጽሐፋቸው የገለጹት፡፡
እ.ኤ.አ. በ1948 የወጣውን የተመድ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃልኪዳን ሰነድ (Universal Declaration of Human Rights) ሙሉ ለሙሉ የተቀበለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን በግልጽ ደንግጓል፡፡ በቃል ኪዳን ሰነዱ በአንቀጽ 19 የሰፈረውን ቃል በቃል በሚመስል መንገድ በአንቀጽ 29 ላይ ሕገ መንግሥቱ አስፍሮታል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የወጡ የፕሬስ አዋጆችና ሌሎች ተዛማጅ ሕጎች ግን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን ለተሰጠው ለፕሬስ ነፃነት አደጋ መፍጠራቸው ለብዙ ጊዜ ሲያወዛግብ ነው የኖረው፡፡ በተለያዩ ጊዜ ከወጡ የፕሬስ ሕጎች በተጨማሪ የፀረ ሽብር አዋጁና የሲቪክ ማኅበራት አዋጅ በመሠረታዊው የሐሳብ ነፃነት ላይ አደጋ አምጥተዋል የሚሉ ስሞታዎች ሲቀርቡ ነው የቆየው፡፡ ኢትዮጵያም ሕጎችን መገልገያ በማድረግ የፕሬስ ነፃነትን እያፈነች፣ ሚዲያዎችን አላንቀሳቅስ እያለችና ጋዜጠኞችን እያሳደደች ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲከተላት ነው የኖረችው፡፡ በሚዲያ ምኅዳር መስፋትና ጥበት ወይም በፕሬስ ነፃነት ዓለም አቀፍ መለኪያ ሰንጠረዦች ላይም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ነጥብ ሲሰጣት ኖራለች፡፡ በዓለም አቀፍ አደባባዮች ላይ አገሪቱ ከሚከተላት ውግዘትና የገጽታ መጠልሸት በተጨማሪም፣ አፋኝ ሥርዓትን ያሰፈነች ናት በሚል የከፋ ማዕቀብና ቅጣት ባይደርስባት እንኳን የገጠማት ጫናና ውግዘት ቀላል አልነበረም፡፡ አንዳንዶች በዚህ የተነሳ በይፋ ኢትዮጵያ ላይ ማግለልና ከበድ ያለ ግፊት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ያስፋ፣ እንዲሁም የሐሳብ ነፃነትን አይገድብ የሚለው ግፊት ተደማምሮ በሕዝቡ ውስጥ የተጠራቀመው የነፃነት ጥያቄ በፈጠረው ተቃውሞ ኢሕአዴግ በመጨረሻ እጅ ሰጠ፡፡ ከሦስት አሥርታት በኋላ ሥልጣን ለቆ አሁን ያለው መንግሥት በቦታው ተተካ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተራማጅ የሚባሉ የፕሬስ ነፃነት ምኅዳርን በሰፊው የከፈቱ ውሳኔዎችን አሳልፎ ነበር፡፡ ጋዜጠኞች፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሰፊው ከእስር ተለቀቁ፡፡ የታፈኑና የተዘጉ ሚዲያዎች በሰፊው ተከፈቱ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋዜጠኛ በእስር ሳይገኝ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀንን በድምቀት ስታከብር ታየ፡፡ የብልፅግና መንግሥት ከዚህ በተጨማሪም የፕሬስ አዋጁን ጨምሮ አፋኝ ሲባሉ የቆዩ ሕጎች እንዲሻሻሉ የሚያደርግ የሕግ ሪፎርም ዕርምጃም ወሰደ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ከሙያውና ከባለሙያው እኩል ራሱ መንግሥት የጠቀመና ዓለም አቀፍ ገጽታውንም ያሻሻለ ዕርምጃ ተብሎ ሲወደስ ነው የቆየው፡፡
የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መውጣት እጅግ ከፍተኛ አድናቆት ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማው በቀረበውና ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር በቂ ውይይትና መግባባት ባልተደረገበት የማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1374/2017 እንዲተካ መደረጉ ከባድ ክርክር አስነስቷል፡፡
የሕግ ሪፎርም ሲካሄድ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር በነበረው ቡድን ውስጥ ተሳታፊ የነበረውና በተለይ የሚዲያ አዋጁን በቅርበት የሚያውቀው ጋዜጠኛና የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጎሹ፣ አዋጁን ገና በሁለት ዓመቱ ወደ ማሻሻል የተገባው በተግባር ተሞክሮ አላሠራ በማለቱ ነው የሚል አመክንዮ በመንግሥት መሰጠቱን አይቀበለውም፡፡ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የራሱን የተጋነነና የተለጠጠ ግምት በመስጠት ስህተቶችን ለመቆጣጠርም ሆነ የዕለት ሥራውን ለመከወን አዋጁ አላሠራ እንዳለው አድርጎ መከራከሩና ወደ አዋጅ ማሻሻያው መገባቱ የተጨበጠ ነገር አይደለም፡፡ በአገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶችን ማጣቀሻ በማድረግ የሚዲያ ሕጉ አሠሪ አለመሆኑ ያመጣቸው ናቸው ብሎ መደምደም በጣም የተለጠጠ ነው፡፡ ሚዲያ አዋጁን ብቻ እንጠቅሳለን እንጂ የሲቪክ ማኅበራት ሕጉም ሆነ ሌሎች የተሞገሱ አዋጆች በአጭር ጊዜ በተግባር የገጠማቸው ተመሳሳይ ዕጣ ነው፡፡ ልክ እንደ ቀደመው መንግሥት ሁሉ ምርጫ ቀረብ ባለ ሁሉ ሕጎችን ማጥበቅና የተለያዩ ዘርፎችን መሸምቀቅ የተለመደ እየሆነ እንዳይመጣ ሥጋት አለኝ፡፡ ከለውጡ ወዲህ ወደ 30 ዓይነት ሕጎችን ነው በሕግ ሪፎርሙ ለማሻሻል የተሞከረው፡፡ ከሕጎቹ በተጨማሪ የተቋማትን ሥራና ኃላፊነት ለማሻሻልም ተሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ውጤት የሚያመጡ የተባሉ ሕጎችን ዳግም በሌላ ዙር በራሱ ወደ ማሻሻል መንግሥት ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ በእኔ ግምት ጥሩ አዝማሚያ አይደለም፤›› የሚል ይዘት ያለው ሐሳቡን አጋርቷል፡፡
ጋዜጠኛ ፋኑኤል በበኩሉ፣ ‹‹የፕሬስ ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ በአስተዳዳር ወይም በሌላ ሕግ ክልከላ የሚደረግበት አይደለም፡፡ አዲሱ የሚዲያ አዋጅ ማሻሻያ የገለልተኛ ቦርዱን ሚና ለሚዲያ ባለሥልጣኑ ሙሉ ለሙሉ ሰጥቶታል፡፡ በአጭር ዓመት ይህን ወደ ማድረግ ከተገባ በቀጣይ ከበድ ያለ ነገር እንደሚመጣ ነው የምገምተው፤›› ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ በርካታ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የፕሬስ ነፃነት ምኅዳር በኢትዮጵያ እንዲሰፋ የሚያስመሠግን ሥራ መሥራታቸው እስከ ዛሬም ይወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን በቆዩበት ባለፉት ስድስት ዓመታት ከአንድ ጊዜ አጋጣሚ በስተቀር ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመገናኛ ብዙኃን ሲሰጡ አለመታየታቸው ትልቅ ግርታን የፈጠረ ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በነበሩበት ወቅት በሁለት/ሦስት ወራት ልዩነት የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን በፈረቃ ተጠርተው በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ መታየታቸው የነበረና ሰርክ የመሪዎች ተግባር ሆኖ የቆየ ልማድ ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ከሚዲያው ጋር ከፈጠሩት ቀረቤታ አንፃር ይህን እንደሚያስቀጥሉትና የበለጠ እንደሚያሳድጉት ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ሲሆን ግን አልታየም፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣናት እንዲሁም የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በቀደመው ጊዜ ከሚዲያው ጋር የተሻለ ቅርርብ ፈጥረው እንደነበርም የዘርፉ ባለሙያዎች ያስታውሳሉ፡፡ ከአቶ በረከት ስምኦን እስከ አቶ ሽመልስ ከማል፣ አቶ ጌታቸው ረዳና ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ድረስ የነበሩ የቀድሞ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣናት የተሻለ ቅርርብ ከሚዲያው ጋር ፈጥረው ነበር በሚል ስማቸው ሲጠቀስ መስማትም የተለመደ ሆኗል፡፡ አሁን ይህ የፖለቲካ ባህል ጠፍቶና በይፋ ጋዜጠኞችን ለመግለጫ መጥራት ተትቶ በሁሉም የመንግሥት ሚዲያዎች በተመሳሳይ ሰዓት የሚሠራጩ ኤዲት የተደረጉና የተመጠኑ የአመራሮች ማብራሪያዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል በማለት ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ሐሳቦችና አገራዊ ጉዳዮች ሚዲያዎች አመራሩን በቀጥታ ለመጠየቅ የሚችሉባቸው ድልድዮች እየተሰበሩ፣ የተከሸነ ቪዲዮ ማሠራጨት አዲስ ባህል እየሆነ መምጣቱን ነው ባለሙያዎቹ በችግርነት የሚያነሱት፡፡
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2024 ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከ180 የዓለም አገሮች መካከል 140ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ይፋ አድርጓል፡፡ ሚዲያ በዓለም ዙሪያ በርካታ ችግሮች ተደቅኖበታል በሚባልበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ ውጤት እንደሌላት ሪፖርቶች ይገልጻሉ፡፡ የአውሮፓ ኅብረት የተሰደዱ ጋዜጠኞች ፈንድ ኃላፊ ፔንሎፔ ዊንተርአገር፣ ‹‹ከዓለም ሕዝብ 70 በመቶው በአምባገነን አገዛዞች ሥር የሚኖር ነው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ደግሞ የፕሬስ ነፃነትን ለመንጠቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው የዘንድሮውን የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት፣ ‹‹ዓለም በግጭትና በመከፋፈል በወደቀበት በዚህ ወቅት የፕሬስ ነፃነትም ከባድ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ የጋዜጠኞች እስራትና እንግልት ጨምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የፈጠረው አደጋ ከባድ ነው፡፡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚመራው የዓለም መረጃ መረብ ለሐሰትና ለጥላቻ መረጃዎች ከመጋለጡ በተጨማሪ የአልጎሪዝም መዛባት ያለው በመሆኑ ለፕሬስ ነፃነት አደገኛ ሁኔታን ፈጥሯል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የሚዲያ ዘርፍ በተለይ የግል መገናኛ ብዙኃን በብዙ አገሮች ኢንቨስትመንትም ሆነ አመቺ የመሥሪያ ዕድሎች ያልተመቻቹለት ዘርፍ በመሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ቢቢሲ ታዋቂውን ሀርድ ቶክ የተባለ ፕሮግራሙን በቅርብ ጊዜ ሥራ አስቁሟል፡፡ እጅግ አትራፊ የሚባለው የፌስቡክ ባለቤት ሜታ ኩባንያ ደግሞ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያጣሩ ፕሮጀክቶችን በመላው ዓለም መደገፉን እንደሚያቆም በቅርቡ አሳውቋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት በርካታ ድጋፎችን በወጪ ቅነሳ ስም እንዲቋረጡ ማድረጋቸው፣ የዓለም ነፃ ሚዲያ ዘርፍ እንቅስቃሴን መጉዳቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በአሜሪካው ድርጅት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ወደ 2000 የሚዲያ ሥራ የሚሠሩ ተቋማት ገንዘብ አጥተው አደጋ ላይ ወድቀዋል እየተባለ ነው፡፡
ላ ሲላ ቫሺያ (La Silla Vacía) የተባለ አንድ የኮሎምቢያ የዲጂታል ሚዲያ ባለቤትና ኤዲተር ሁአኒታ ሊዮን፣ ‹‹ጋዜጠኝነት ዛሬ ላይ በዓለማችን ልክ ታይታኒክ መርከብ እየሰመጠች ሳለ ቫዮሊን እንደሚጫወቱት ሙዚቀኞች ሆኗል፡፡ መርከቡ እየሰመጠና ሰዎች እያለቁ እስከመጨረሻው እንደ ሞዘቁት ከያኒያን ሙያው ቀስ በቀስ እየሞተ ጋዜጠኞችም ቫዮሊን እየተጫወቱ ይገኛሉ፤›› በማለት ነበር የዓለም የፕሬስ ነፃነት ይዞታ የተጋረጠበትን አደጋ የገለጸችው፡፡