ዘንድሮ 47 ቢሊዮን ብር የከሰረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ትርፋማነት እንደሚሸጋገር የኩባንያው ኃላፊዎች ገለጹ
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ኪሳራ ቢያጋጥመውም፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፋማነት ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የእናት ኩባንያው ኃላፊዎች ተናገሩ። መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ሳፋሪኮም ኩባንያ፤ እስከ መጋቢት ወር ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ካገኘው 3 ቢሊዮን ዶላር የአገልግሎት ገቢ 10 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገበያ ድርሻ እንደሆነ አስታውቋል።
ኩባንያው የሚመራበት በጀት ዓመት መጠናቀቁን በማስመልከት ባለፈው ሐሙስ ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገቢ ባለፈው ዓመት 2.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ 7.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ270 ፐርሰንት እድገት ቢያሳይም፤ 47 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኪሳራ እንደገጠመው ዋና ስራ አስፈጻሚው ዊም ቫንሔለንፑት ገልጸዋል።
“ይህ ኪሳራ በአብዛኛው ኩባንያው በሚገኝበት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ ከምንጠብቀው ጋር የተስማማ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ ያደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጥ በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ጠቁመዋል።
የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጡ፤ በአጭር እና መካከለኛ ጊዜ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም “እርምጃዎች መወሰዳቸውን” የሳፋሪኮም ኃላፊዎች አብራርተዋል። እርምጃው በውጭ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተቀጠሩ የውጪ ሀገር ዜጎችን መቀነስን የካተተ ነው።
🔴ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15849/