በኦሮሚያ ወደ አዳማ/ናዝሬት የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ታገቱ

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በአርሲ ስሬ ወረዳ ዛሬ ረፋዱ ላይ ታጣቂዎች አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አስቁመው ከ50 በላይ ተሳፋሪዎችን አግተው መወሰዳቸውን ታውቋል። ታጣቂዎቹ እገታውን የፈጸሙት፣ ተሽከርካሪው ከአርሲ ስሬ ወረዳ ወደ አዳማ ከተማ በመጓዝ ላይ ሳለ እንደሆነ የአካባቢው የዓይን እማኞች ተናግረዋል። እገታው የተፈጸመበት ሥፍራ ከዚህ ቀደም በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ ይደረግለት እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ በዛሬው ዕለት ግን የጸጥታ ኃይሎች ከአካባቢው ተነስተው እንደነበር ገልጸዋል። ታጣቂዎች፣ በዞኑ በአቦምሳ ወረዳ ልዩ ስሙ ከሬቸር በተባለ ሥፍራ ባለፈው እሁድ በተመሳሳይ ወደ አዳማ/ናዝሬት ከተማ ሲጓዝ ከነበረ ተሽከርካሪ ላይ በርካታ ተሳፋሪዎች እንዳገቱም ምንጮች አስረድተዋል።