የምርመራ ዘገባ ጫንጮ ላይ የከተሙ ‘ሪጴ ሎላ’ የተባሉ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አባላት አነጋጋሪ ድርጊት ላይ ምርመራ አርገናል
(መሠረት ሚድያ)- ከአዲስ አበባ 40 ኪ/ሜ ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው የጫንጮ ከተማ ከቅርብ አመታት ወዲህ ሰላም ርቋታል። ተስማሚ አየር እና መልካም ገፀ ምድር ያላት የኦሮሚያ ክልሏ ጫንጮ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለው) እና በመንግስት ሀይሎች መካከል በሚደረግ ግጭት ምክንያት ፀጥታዋ ደፍርሷል።
ታድያ በከተማዋ ተወልደው ያደጉትም ይሆን ከሌላ ቦታ ወደ ከተማዋ ሄደው የሚኖሩ ነዋሪዎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ‘ሪጴ ሎላ’ በተባሉ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አባላት አበሳቸውን እያዩ እንደሆነ መሠረት ሚድያ ባደረገው ክትትል ደርሶበታል።
“የምኖረውም ተወልጄ ያደኩትም እዚሁ ጫንጮ ከተማ ነው፣ ለስራ የተሰማራሁትም በሞባይል ሽያጭ ላይ ነው” የሚለው አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ነዋሪ ሰሞኑን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተማውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ እነዚህ ‘ሪጲ ሎላ’ የተባሉት የመንግስት ሀይሎች የጫንጮን ነዋሪ እያሰቃዩ እንደሆነ ይናገራል።
“እኔ ላይ የደረሰውን ለመናገር፣ አንድ ቀን ሶስት ሆነው መጡና ብር አምጣ አሉኝ። ካሽ የለኝም ስላቸው ‘ካዝና ውጥ ይጠፋል? እናየዋለን!’ ሲሉኝና ሲቆጡ የእቁብ ብር ነው ስል አንዱ በጥፊ መታኝና 3,000 አርግ አለኝ፣ ሰጠኋቸው። የሆነውን ለጓደኞቼ ስናገር እኔንም፣ እኔንም 4,000 ብር ምናምን ወሰዱብን አሉኝ” በማለት ሁኔታውን አስረድቷል።
ይህን ተከትሎ የጫንጮ ከተማ የፀጥታ ሀላፊ ጋር ሄደው ሲያመለክቱ “ከአቅማችን በለይ ነው፣ የኛን ፖሊስ ራሱ ደበደቡብን፣ ዝም በሉ በቃ” ብሎ ምላሽ እንደሰጣቸው አክሎ ተናግሯል።
ሚድያችን ያሰባሰበው መረጃ እንደሚጠቁመው ‘ሪጴ ሎላ’ የተባሉት ልዩ ሀይሎች “እኛ ባንኖር ማንም ይዘርፋችሁ ነበር” በማለት ሆቴሎች ውስጥ እየበሉ እና እየጠጡ ሳይከፍሉ ይወጣሉ፣ በየግለሰቦች ቤት እያንኳኩ ገንዘብ አስገድደው ይወስዳሉ፣ ከትንንሽ ሱቆች ጀምሮ ያሉትን የፈለጉትን እቃ በግድ ይቀበላሉ።
ሌላኛው ምንጫችን ደግሞ የደረሰበትን ሲያስረዳ “ከቀናት በፊት ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ላይ መጡና እቃ ግዛኝ አሉኝ፣ እኛ አዲስ እቃ እንጂ አሮጌ ስለማንይዝ አሮጌ አንገዛም ብለን ምላሽ ስንሰጥ ሄዱ። ወዲያው ልዩ ሀይሎቹ አንዳንድ ቤቶች እየዞሩ ንብረት እየወሰዱ ነው የሚል ወሬ ስንሰማ በፍጥነት ውድ ውድ እቃዎችን ደበቅን፣ እንደፈራሁት ከ30 ደቂቃ በኋላ የሱቁ ባለቤት ማነው ብለው መጡ። አቤት ስል የ21,000 ብር ግምት ያለው እቃ አነሱ፣ እምቢ ስል በሰደፍ መታኝ” ብሎ የደረሰበትን አስረድቷል።
አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የከተማው አመራር “ሆቴሎች ሁሉ የገባቸው ናቸው፣ ያሉትን ያደርጋሉ። ሌላ ሰው መንገድ እያስቆሙ እስከ 8,000 ብር እንደሚቀበሉ እንሰማለን” ብለው ተናገረዋል።
“ተወልጄ ባደኩበት፣ ተመርቄ የተወሰነ አመት የመንግስት ቢሮ በሰራውበት ከተማ እንዲ ካረጉኝ ሌላውማ ፈርቶ ዝም ብሎ ነው ያለው” የሚለው ባለሱቅ መከላከያ ከወጣ በኋላ የፈለጉትን ቢያደርጉ ማንም እንደማይናገራቸው ተናግሯል።
መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርዬ ከኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።