” በጀት በመከልከልና በማስከልከል የሚደናቀፍ ትግል አይኖርም ! ” – እናት ፓርቲ
እናት ፓርቲ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው ላይ ያሳለፈውን የበጀት ክልከላ ” ፖለቲካዊ ውሳኔ ” ሲል ጠርቶት አውግዟል።
“ በጀት በመከልከልና በማስከልከል የሚደናቀፍ ትግል የለም “ም ብሏል።
እናት ፓርቲ ምን አለ ?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር በጻፈው እና ለፓርቲው ግልባጭ በተደረገ ደብዳቤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለፓርቲው በ2016 ዓ.ም የተሰጠን ድጋፍ ብር 1,702,561.65 (አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ኹለት ሺህ አምስት መቶ ስድሳ አንድ ከ65/100) ኦዲት ማድረጉን አመልክቷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቀጥታ የኦዲት ሪፖርቱን ለኦዲት ተደራጊ እናት ፓርቲ እንዳላደረሰና ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ፓርቲው ጋር መምጣቱን ገልጿል።
የኦዲት ግኝት ተብሎ በዋነኛነት የቀረበውና ትልቅ ጥያቄ ያስነሳው ፓርቲያው ከተደረገለት ድጋፍ ፦
- በጎፋ ዞን ለተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ብር 20,000.00 (ሃያ ሺህ ብር) መለገሱ ፤
- ለአንድ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ስንብት ለማስታወሻ ብር 15,000.00 (አሥራ አምስት ሺህ ብር) ወጪ ማድረጉ፤
- የፓርቲያው የላዕላይ ምክር ቤት አባል ከዚኽ ዓለም በሞት በተለዩበት ወቅት ለባነር ማሠሪያ የወጣ ብር 3,500.00 (ሦስት ሺህ አምስት መቶ ብር) በድምሩ ፓርቲው ብር 38,500.00 (ሠላሳ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር) ” ከታለመለት ዓላማ እና ተግባር ውጭ ያወጣ መኾኑ” መመላከቱን አስረድቷል።
በዚህም ምክንያት ቦርዱ በዚህ ዓመት ፓርቲው የሚሰጠውን የመንግሥት ድጋፍ ሊያገኝ እንደማይገባ መወሰኑን ፤ የፓርቲውን ሂሳብ በጣምራ በሚያንቀሳቅሱት 3 አመራሮች ላይ ፌዴራል ፖሊስ ምርመራ እንዲያደርግ መወሰኑን በደብዳቤ እንደገለጸለት ጠቅሷል።
እናት ፓርቲ የቦርዱ ውሳኔ ” አላግባብ ወጣ ” ስለሚለው 38,500.00 ብር ሳይሆን ከጀርባው ሌላ ጉዳይ እንዳለው እገምታለሁ ብሏል።
” አላግባብ ወጣ ” የተባለው ወጪ ፦
➡️ ብር 20,000 የመሬት መንሸራተት ለደረሰባቸው ወገኖች የወጣ እጅግ አነስተኛ ገንዘብ መሆኑና ይህም የነገ መራጮቹን ጎን ለሚጠይቀው የስብዕና ሞራል መቆም ከማስፈለጉ አኳያ ሊደረግ ከሚችል በጣም አነስተኛው ነገር እንደሆነ፤
➡️ ምንም ክፍያ ሳይከፈላቸው ለሀገራቸውና ሕዝባቸው ለመታገል ጊዜያቸውንና መላ እነሱነታቸውን ሰጥተው ለአደጋ ጭምር ራሳቸውን አጋልጠው የመጓጓዣ ወጪያቸው እንኳን ሳይሸፈን ለሀገር ከመቆም አኳያ በፓርቲው ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ከፓርቲው በሞት እንዲኹም በአካል ሲለዩ ወጣ የተባለው ወጪ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑንና ከአግባብ ውጭ የወጣ ነው ብሎ እንደማያምን ገልጿል።
ከፓርቲው አመራር ቀብር ጋር ከተያያዘው ብር 3,500 ውጪ ሌሎቹ የተፈጸሙት ወጪዎች በፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚና መላ መዋቅሩ ውሳኔ መሠረት እንደሆነ ጠቁሟል።
ይህ ሆኖ ሳለ ” አመራሮችን በተለየ መልኩ ተጠያቂ ለማድረግ የተኬደበት ርቀት ትናንት የፓርቲ አመራሮችና አባላት እሥርና አፈና ሲገጥማቸው ባሉበት ድረስ በመሄድ ያጽናና እና ለማስፈታት ግብ ግብ ይገጥም የነበረ ቦርድ በቅጽበት እንዲህ የመውጊያ ስለት አቀባይ ወደመሆን ያሽቆለቆለበት ቅጽበት ያስገርማል፣ ያሳዝናልም። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይመዘግባል ” ብሏል።
የተጠቀሰው ገንዘብ ፓርቲው በድጋፍ ከተሰጠው ገንዘብ ወጪ እንዲደረግ ያስገደደው ምክንያት በወቅቱ ፓርቲው ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚጠቀምበትና ከአባላትና ደጋፊዎች የሚሰበሰብ ገንዘብ ከተቀመጠበት የባንክ ሒሳብ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉና ገንዘቡ በወቅቱ ወጪ መደረግ የግድ ስለነበረ እንደሆነ አመልክቷል።
ነገር ግን የማኅበራዊ አገልግሎት የባንክ ሂሣቡን ማንቀሳቀስ በቻለበት በአሁኑ ሰዓት ግን የተጠቀሰውን በውንጀላ የተያዘበትን ገንዘብ ብር 38,500 አዛውሮ ዝግጁ ያደረገና ለመመለስም የሚችል መሆኑን ለፌዴራል ዋና ኦዲተር በፈረመው መተማመኛ ጽሑፍ መስጠቱን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲው ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ወደሥራው ባተኮረበት ወቅት ከዚህ ቀደም ‘ ፓርቲውን ከመፍረስ ለመታደግ በሚል ከፓርቲው የተቆረጠ ኃይል ” ፓርቲውን በጀት አስከለከልኩ” ፣ ” እነ እከሌንና እከሊትን ላሳስር ነው ” እያለ ለተለያዩ ግለሰቦችና ሚዲያ አካላት ወሬ እየነዛ መመልከቱን በዚህም ” በሬ ከአራጁ ” ለማለት መገደዱን ገልጿል።
ይህን አካል ከነዝርዝር ማንነቱ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ጠቁሟል።
ፓርቲው የመንግሥትን ሥልጣን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመጨበጥ እንደሚሰራ ገልጾ የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ እያንዳንዷ ሳንቲም ተጠያቂነት ባለው መልኩ ብቻ መውጣት እንዳለባት እንደሚያምን ለዚህም ተግቶ እንደሚሰራ ፤ ኦዲት መደረጉም እንደሚያስደስተው ገልጿል።
ነገር ግን የኦዲት ግኝት ተብሎ ነቀረበውና ቦርዱ ያሳለፈው ውሳኔ ከአስተዳደራዊ ውሳኔነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ግብ ያዘለ ነው ብሎ እንደሚያምን አመልክቷል።
” በቦርዱ ውሳኔ ላይ ዕለት ከዕለት የሚያስጨንቀንና ዘወትር የምንጮኽለት ወዲኽም ግራ ቀኝ ጥርስ ያስነከሰብን የሕዝባችን ስቃይ ከቀለለና ጊዜ ከተረፈን እንደአስፈላጊነቱ ሕጋዊ መንገድ ተከትለን ይግባኝ እንልበት ይሆናል ” ብሏል።
ፓርቲው አለኝ ባለው መረጃ እንዳይሰጠው የታገደው የ2017 የበጀት ድጋፍ ብር 600 ሺህ ገደማ መሆኑን ጠቁሟል።
” በጀት በመከልከልና በማስከልከል የሚደናቀፍ ትግል አይኖርም ” ሲልም አሳውቋል።