አምነስቲ መንግሥት በሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት የለውም አለ

በኢትዮጵያ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝና ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን መንግሥት እንደሚክድ፣ በሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአገሮችን የሰብዓዊ መብት ቁመና በተመለከተ ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን በትጥቅ የታገዘ ግጭት ከሚካሄድባቸውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰዎች ሕይወት ከተቃወሰባቸው ኢራቅ፣ ሱዳን፣ ምያንማር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያና ዩክሬን የመሳሰሉ አገሮች ተርታ መድቧታል፡፡

አምነስቲ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ባለ410 ገጽ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግሥታቸው፣ በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እየተፈጸሙ ያሉ ከሕግና ከፍርድ ቤት ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እየካዱ ነው ብሏል፡፡ ፍትሕ ለማስፈን ተፈጸሙ የሚባሉ ወንጀሎችን ከመካድ ባለፈ መንግሥት ትርጉም ያለው ዕርምጃ አለመውሰዱን አስታውቋል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣነት ወንጀል የፈጸሙ አካላት በሕግ መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንደማይወስዱ፣ ተጎጂዎች እውነትና ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን መነፈጋቸውን ገልጿል፡፡

በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ ከሚፈጸም ፆታዊ ጥቃት በተጨማሪ፣ ከግጭት ጋር የተገናኙ ፆታዊ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ በጅምላ የማሰር ድርጊት መኖሩን፣ ነገር ግን የመንግሥት አካላት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎችን በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የሚደነግገውን የኢትዮጵያን ሕግ መፈጸም እንደማይችሉ አብራርቷል፡፡

በአማራ ክልል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ሕጎች እየተጣሱ መሆናቸውንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር ለመገናኘት ወደ ውጭ ከሄዱ በኋላ ሲመለሱ ማስፈራሪያና ዛቻ ይገጥማቸዋል ብሏል፡፡ የመብት ተሟጋቾ በተጓዙባቸው አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚያደርሱባቸው በአምነስቲ ሪፖርት ተካቷል፡፡

መንግሥት በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት ተሰንደው የሚቀርቡ የመብት ጥሰት ወንጀሎችን እንደሚያጣጥል፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ፍትሕን ዕርቅ ላይ ያተኮረ ወረቀት ላይ የቀረ ጉዳይ ነው ብሎታል፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናት የመናገር ነፃነትና በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብት ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ማዋከብና ማስፈራራት፣ በአማራ ክልል ኢንተርኔት ማቋረጥ ላይ መሳተፋቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በአምነስቲ ሪፖርት ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና አርቲስቶች፣ በኃይል በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉና የተወሰኑት አገር ለቀው መሰደዳቸው ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ ጆርጂያ፣ ሃንጋሪ፣ ኪርጊዝታንና ኒካራጓን ጨምሮ የመደራጀት መብት ከተገደበባቸው 15 አገሮች ኢትዮጵያም ተመድባለች፡፡

በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚዲያ ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የገጠማቸው ተጎጂዎች ፌስቡክን ተጠያቂ ለማድረግ የጀመሩት ጥረት በአዎንታዊ የሚወሰድ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህ ቀደም ተደፍራ የተገደለችው የሰባት ዓመት ሕፃን ፌቨን አወት በሴቶች ላይ የቀጠለ ፆታዊ ጥቃት መኖሩን ማሳያ ናት ብሏል፡፡

በመንግሥት ኃይሎችና በታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ ሕገወጥ ጥቃቶችና ግድያዎች ከታዩባቸው 11 አገሮች መካከል የተመደበችው ኢትዮጵያ፣ በአየር ላይ ድብደባና በድሮን የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአገሮቹ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት የአፍሪካ የሰብዓዊ የሰዎች መብት ኮሚሽን የቴሌ ኮሙዩኒኬሽንና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳይቋረጥ ያደረገውን ጥሪ ችላ ካሉ አሥር የአፍሪካ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ የተመደበች ሲሆን፣ የአገልግሎቱ መቋረጥ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉሏል ሲል ወቅሶ ነበር፡፡