ጌታቸው ሽፈራው ፡ በደርግ ወቅት ወጣቶች በግድ እየታፈኑ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ይወሰዱ ነበር። በዚህ መጠን ህፃናትን ግን አልነበረም። የዞን ኮሙኒኬሽን ገፅ ሳይቀር በይፋ የሚለጥፈውን ተመልከቱ። ህፃናት በግዳጅ ከደርግ በከፋ አፈሳ እየተወሰዱ ነው።

እንዲህ ነው የሚያደርጉት!
1) በችግር ጎዳና የወጡ ህፃናትን ይይዟቸዋል። አንድ ሰሞን ትምህርት ቤት ወይንም ሌላ ቦታ ያሰነብቷቸዋል።
2) የቆሎ ተማሪዎችን በቡድንም ሆነ በተናጠል ሲሄዱ ይይዟቸዋል።
3) እረኞችን፣ ተማሪዎችን ይይዟቸዋል።
4) በቤተሰቦቻቸው ችግር ምክንያት ገና በለጋ እድሜያቸው በመኪና ረዳትነትም በሌላም ስራ የተሰማሩትን ይይዟቸዋል።
በሌላም ሁኔታ ያሉትን እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱትን በግድ አፍነው አንድ ማዕከል ያሰነብቷቸዋል። ከዛም ኮታዬን አሟልቻለሁ ብለው ያስረክባሉ።
ይህ ከደርግ የባሰ ህፃናትን ለውትድርና መመልመል ስልጣናቸውን የሚታደግ መስሏቸዋል። ህዝብ አገር ለመከላከል ሲሆን ልጁን መርቆ ይሰጣል። ህፃን ልጁን ወደ ግድያ ሜዳ የሚወስደውን እንደሚታገለው ግን አላሰቡበትም። አሁን ህፃን ልጁ እንደሞተ ነው የሚቆጥረው። ደመኛው ደግሞ አገዛዙ። ይህ ልጁ የተወሰደበት አባት ብቻ ምሬትና እርምጃ አይሆንም። የሞራል ልኬትን፣ የልጅን ሁኔታ የሚያውቀው ሁሉ የሚጋራው ስሜት ይሆናል።

ከብቶቹን በሰላም አውሎ ይመጣል ብሎ የሚጠብቀውን ልጁን፣ ተምሮ ይመለሳል ብሎ የሚጠብቀውን ልጁን፣ ሱቅ ተልኮ ይመለሳል የተባለውን ልጁን፣ ከተማ ሄዶ ይመለሳል ብሎ የሚናፍቀውን ልጁን…በዚህ መንገድ በጥጋብ ተነጥቆ “ይሁና” ብሎ የሚተው አባትም ሆነ ህዝብ የሚኖር ይመስላቸዋል። ይህ የአገዛዙ አረመኔነት የነበሩትን እሳቶች ያቀጣጠላል እንጅ እድሜያቸውን የሚያራዝም ከመሰላቸው የምርም ስተዋል ማለት ነው።