ሩሲያ የናዚ ጀርመን በሁለተኛው የአለም ጦርነት በይፋ የተሸነፈበትን 80ኛ አመት የድል በዓሏን አክብራለች።
በድል በዓሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና የቻይናውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ተሳትፈዋል።
በተጨማሪ የቡርኪናፋሶው መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ በፕሬዚዳንት ፑቲን ግብዣ የግል አውሮፕላን ከሞስኮ ተልኮለት በፕሮግራሙ እንዲሳተፍ ተደርጓል።
መሪዎቹ ትናንት በክሬምሊን የእራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን ዛሬ በዓሉ በአደባባይ በወታደራዊ ትርዒቶች ተከብሯል።
የዛሬው ወታደራዊ ሰልፍ ሞስኮ ወደ ዩክሬን ጦሯን ካዘመተች በኋላ ትልቁ ነው ሲባል ከ10 አመታት በኋላ የበርካታ ሃገራት መሪዎች የተገኙበትም ነው ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ባደረጉት ንግግርም በአሁኑ ወቅት በዩክሬን እየተፋለሙ ያሉ የጦር ሰራዊታቸውን አሞግሰዋል።
በወታደራዊ ሰልፉ ላይ ከ11,500 በላይ ወታደሮቼ እና ከ180 በላይ ወታደራዊ መኪኖች ተካፋይ ሆነዋል።
የሩሲያ የአየር ኃይል ቡድንም የአየር ላይ ትርኢቶችንም አሳይተዋል።
የፑቲን የውጪ ጉዳይ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ይህንን የጋራ በዓላችንን በማስመልከት ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሃሳብ መለዋወጣቸውን እና የእንኳን አደረሰህ መልዕክት እንደተለዋወጡ ለሚዲያዎች ገልፀዋል።
ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ንቁ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን ከ21 ሚሊየን ሰዎች በላይም በጦርነቱ አጥታለች።
የናዚ ጀርመን በይፋ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የተሸነፈበትን ምክንያት በማድረግ ሩሲያ ቀኑን እንደ ድል በዓል የምታከብር ሲሆን ዘንድሮ 80ኛ አመቱን እያከበረች ትገኛለች።
Source: AP , Sputnik