በኢትዮጵያ ኢመደበኛ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑ፣ መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ ቀንድ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ተነገረ፡፡
‹‹የከተሞች መደበኛ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ገጽታዎችና የአስተዳደር ቅኝት›› በሚል መሪቃል በተዘጋጀው መድረክ፣ ‹‹የከተሞች መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ ገጽታና ባህሪያት በኢትዮጵያ›› በሚል ሐሳብ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት መካነ ጥናት ኮሌጅ አባል ቻላቸው ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ‹‹58 በመቶ የዓለማችንን የሥራ ዕድል የሚፈጥረው መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ ነው፤›› ብለዋል።
ለታዳጊ አገሮች 84 በመቶው የሥራ ዕድል የሚፈጠረው ከዚሁ ዘርፍ እንደሆነ በማስረዳት፣ ሴቶችና ሕፃናት ደግሞ መደበኛ ባለሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንዳላቸው ገልጸው፣ ያገቡ ወይም አግብተው የፈቱ ሰዎች ደግሞ በዚህ ዘርፍ በአብዛኛው ሲሳተፉ ይስተዋላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚፈልሰው የሰው ኃይል የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉም አክለዋል። የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ አጠቃላይ ገቢ አንድ ሦስተኛና ከዚያ በላይ የሚሆነው የሚመነጨው ከዚሁ ዘርፍ መሆኑንም አመላክተዋል።
እ.ኤ.አ ከ1992 እስከ 2000 ድረስ ያሉ የጥናት ውጤቶች በአማካይ የሚያመላክቱት ይኼን ነው ብለዋል። ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ እያደገ መምጣቱ በጥናቱ ተጠቁሟል። በከፍተኛ ደረጃ የሚታየውን የከተማ ሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የሥራ ዕድል መንግሥት መር የሆነው ኢኮኖሚ መሸከም እንዳልቻለም፣ በዚህም ዜጎች በቀጥታ ወደ መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ ዘርፍ እንደሚገቡ ገልጸዋል
‹‹የከተሞች መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል ሐሳብ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ ጌታሁን ፈንታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአገር ደረጃ መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚውን የሚመለከቱ ቀጥተኛ የሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አለመኖራቸውን በጥናታቸው ገልጸዋል።
አሁን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከመደበኛ ያልሆነ ወደ መደበኛ ሽግግር ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ ጉዳይ ለማስፈጸም የቢሮክራሲው ጉዳይ መብዛት፣ ውስብስብ የታክስ አከፋፈል መኖር፣ ለመነሻ የሚሆን ካፒታል ዕጦት፣ የሕግና መመርያዎች ተለዋዋጭነት፣ የብድር አቅርቦታቸው የተገደበ መሆን፣ ሊጣል ከሚችል የታክስ ክፍያ አንፃር ያሉ ፍራቻዎች ለሽግግሩ ተግዳሮቶች ተብለው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ጌታሁን (ዶ/ር) በጥናታቸው ጠቁመዋል።
ለአብነት ያህል 58 በመቶ የአዲስ አበባ ዕድገት የሚመጣው በፍልሰኞች መሆኑን የገለጹት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ 90 በመቶ ፍልሰተኞች የሚቀላቀሉት መደበኛ ያልሆነውን ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ነው ብለዋል። የፍልሰት መቀጠልና መደበኛ ኢኮኖሚውም በበቂ ሁኔታ የሥራ ዕድል መፍጠር ካልቻለ፣ ዜጎች አማራጫቸው የሚያደርጉት መደበኛ ያልሆነውን የንግድ ዘርፍ ስለሚሆን ማስቀረት እንደማይቻል አስረድተዋል።
በመድረኩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ዳሮት ጉመአ ይገኙበታል። ‹‹መታወቂያ ማውጣትና ማሳደስ በጣም አስቸጋሪ ነው። አገልግሎቱን የሚሰጡ የመንግሥት አካላት ዜጎችን በእኩልነት የሚያስተናግዱበት አሠራር የለም፤›› ብለዋል።
‹‹ይህን ሲያደርጉም የሚጠየቁበት አሠራር ስለሌለ በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት የገዥው ፓርቲ ትስስር (Affiliation) ላላቸው በብቸኝነት እየተሰጠ ንግዱን ወደ እነሱ ማዞር በመጨረሻ ይመጣል። ይህ ችግር እንዴት ነው የሚታየው?›› ሲሉ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት መምህር አስናቀ ከፋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የአዲስ አበባ መታወቂያ የግዴታ መሥፈርት ከሆነና የአዲስ አበባ መታወቂያ ከሌላችሁ አትሥሩ ከተባለ በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል፤›› ብለዋል። አዲሱ ብሔራዊ የፋይዳ መታወቂያ (National Id) አማራጭ ሊሆን ይችላል ሲሉም ገልጸዋል።
‹‹ይህንን የሚያስፈጽሙ አካላት እንዲሞዳሞዱ ሊያደርግ ስለሚችል፣ የከተማ አስተዳደሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።
ጌታሁን ፈንታ (ዶ/ር)፣ ‹‹እንደ ጣሊያንና ጀርመን ባሉ አገሮች የተሰማሩ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች የአንድ አካባቢን ሳይሆን እኛ ብሔራዊ መታወቂያ የምንለውን የሚጠቀሙበት ልምድ አለ፤›› ብለዋል።
‹‹በተለይ በቅርብ ጊዜ ወደ ከተማዋ የገቡ ፍልሰተኞች መታወቂያ የማይኖራቸው ከሆነ እንዴት ነው የሚሆኑት? በዘርፉ የሚሰማራ ማንኛውም ዜጋ ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ ተብሏል። ይሁን እንጂ በነባራዊ ሁኔታው የሚታየው ከዚያ በታች ዕድሜ ያሉ ሲሠሩም ነው። እነሱስ እንዴት ነው የሚደረጉት የሚለው መመለስ አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል። ስለዚህ የታደሰ የአዲስ አበባ መታወቂያ ከሚሆን ብሔራዊ ፋይዳ መታወቂያ ቢሆን እንደሚመረጥ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ እየተቀረፀ ባለው መደበኛ አገራዊ የንግድ ፖሊሲ ውስጥ እንዳልተካተተ ገልጸዋል። ‹‹ሁሉም ሰው ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ እንዲገባ ነው የሚፈለገው፣ ግን ኢመደበኛ ንግድን ማጥፋት እንደማይችል ከተገነዘብን በኋላ ደንብ ቁጥር 88/2009 ወደ ማሻሻል ነው የተገባው፤›› ብለዋል።
በዚህም ዘርፉ እንደ አገር ዕውቅና ሳይሰጠው የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ማድረጉ ዋጋ ሊያሰጠው እንደሚገባ፣ ከዚህ ቀደም አንዱ አባራሪ ሌላኛው ተባራሪ የነበሩበትን ሁኔታ አስቀርቶ ወደ መደበኛ የሚገቡበትን ሥርዓት ማመቻቸቱ እንደ እንደ ጥሩ ዕድል ሊቆጠር ይገባል ሲሉም አክለዋል።
‹‹መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ›› ይረዳ ዘንድ በተዘጋጀው ደንብ ቁጥር 184/2017 ላይ ወደ 68,700 ያህል ሰዎችን ስናወያይ፣ በተደጋጋሚ ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ የሆነው የመታወቂያ ጉዳይ ዛሬም ተነስቷል፤›› ብለዋል። ‹‹ብዙ መወዛገብ ያለብን አይመስለኝም፣ ምክንያቱም የአገራችንን አሁናዊ ሁኔታ ሁላችንም እናውቃለን፣ የከተማው አስተዳደሩ በራሱ በጀት የሚተዳደር ነው። ኃላፊነት የተሰጠውም ነዋሪዎች እንዲያገለግል ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል፤›› በማለት አብራርተዋል።
‹‹ካቢኔ ሲወስን ግልጽ ነው ብሔራዊ መታወቂያ (National Id) ነው ያደረገው። ምንም ብዥታ የለውም፣ ይሁንና ከሚኖርበት ወረዳ የነዋሪነት ማረጋገጫ ማምጣት ይኖርበታል፤›› ሲሉ አክለዋል።
‹‹ነዋሪ መሆኑን ማረጋገጥ ግዴታ ነው፣ ምክንያቱም እጃችንን ላይ ያለው አነስተኛ ሀብት ነው፡፡ ከተማው ለሁሉም አላፊ አግዳሚ ቦታ ማመቻቸት አይችልም። በፍልሰት ለሚመጣ ሁሉ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል።
በዚሁ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ ሐሳብ መምጣቱ ጥሩ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ‹‹ምንም ሥጋት አይግባዎት ማለት እፈልጋለሁ። ለብልፅግና ፓርቲ አባላት ብቻ ዕድል ለመፍጠር ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይህንን ዘርፍ ለመምራት እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቢሮው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ላይ ለሚሰማሩ ነጋዴዎች የአቅም ግንባታ፣ በአነስተኛ ወለድ የሚታሰብ መነሻ ካፒታል ብድር እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል። የአዲስ አበባን ንግድ ሥርዓትን ለማዘመን ዳሰሳዊ ጥናት በማድረግ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።