በኢትዮጵያ ሺሻን በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ የለም፣ ለንግድ አላማ ማስጠቀም ግን ህጉ ይከለክላል

ሺሻ (ሁካ)ማጨስ በህግ ያስቀጣ ይሆን?

⚫ “በኢትዮጵያ ሺሻን በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ የለም፣ ለንግድ አላማ ማስጠቀም ግን ህጉ ይከለክላል ” የህግ ባለሙያ

በኢትዮጵያ ምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን አስተዳደር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1112/2011ዓ.ም #ሺሻን በግል ማጨስ ወይም መጠቀምን #አይከለክልም።

ሆኖም የኢትዮጵያ ምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 በወጣው የሺሻ ምርት ማስመጣት፣ ማጨስና መጠቀም ከ3 ወር እስከ 3 አመት ቅጣት እንደሚጣልበት ይደነግጋል።

አዋጁ ከወጣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።

የህግ ባለሙያው ሳሙኤል ግርማ በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2011 ዓ.ም የፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1112 ሺሻን ማስመጣት፣ ማስጠቀም፣ ለንግድ ስራ ማዋል እና ለ3ኛ ወገን አሳልፎ መስጠት ብቻ በህግ እንደሚያስጠይቅ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ” በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ አለመውጣቱ በሀገር ኢኮኖሚ እና በማህበረሰቡ ጤና ላይ ትልቅ ተፅዖኖ እየፈጠረ ነው” የሚል ሀሳብ ያነሳሉ።

አክለውም ፥ ” ብዙ ሰዎች ሺሻ መጠቀምን የሚከለክል ህግ የለንም ይላሉ ነገር ግን በግል መጠቀምን አይከልክል እንጅ ሁለት ሶስት ሆኖ በመኖሪያ ቤት ውስጥ እና በንግድ ቤት ማጨስ አይቻልም። ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲጠቀም የተገኘ ግን በህጉ ያስጠይቀዋል ” ብለዋል።

የቅጣት እርከኑ በምንድን ነው የሚለያየው?

የህግ ባለሙያው ሳሙኤል ” የወንጀል ቅጣት ሥነ-ስርዓት የራሱ የሆነ መጥሪያ ፍርድ ቤት ያወጣው እርከኖች አሉ። ቅጣት ማቅለያ ተብሎ የሚያዝላቸው ቤተሰብ አስተዳዳሪ እና ጥፋቱን ያመነ ከሆነ ዝቅተኛ ቅጣት ነው የሚጣልበት ” ብለዋል።

አያይዘውም ፥ ወንጀሉን ሲፈፅም የተገኘ ሰው ከዚህ ቀደም በማስጠንቀቂያ የታለፈ ሆኖ በድጋሜ ከተገኘ፣ ህፃናትን እና ተማሪዎችን የሚያስጠቅም ከሆነ ግን ቅጣቱ ከፍ ሊል እንደሚችል አስረድተዋል።

ሺሻን በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ አለመኖሩ ጉዳቱ ምንድን ነው ?

ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸውን የሰጡን የህግ ባለሙያው ” በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ አለመኖሩ ሰዎችን ለማስጠቀም ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሯል፣ ምክንያቱም አንድ ሰው ለእራሱ አስመስሎ በተለያዩ አፖርታማዎች ተሰባስበው እንድጠቀሙ ያደርጋል። ይህ ደግሞ  በማህበረሰብ ጤና እና በወጣት ሃይል ላይ አሉታዊ ተፆዕኖ ይኖረዋል” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የወጣው አዋጅ የሚበረታታ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በግል መጠቀምን የሚከለክል ህግ  አለመውጣቱ ወንጀሎችችን ለመቆጣጠር ክፍተት የሚፈጥር በመሆኑ አዋጁ ሊሻሻል ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን አካፍለውናል።