የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ የታገቱ ኢትዮጵያውያንን አስለቀቀ

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ፣ 17 ታዳጊዎችን ጨምሮ 44 ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ጁሃንስበርግ ከተማ ውስጥ ከፍቃዳቸው ውጭ ከተያዙበት ቤት ዛሬ መታደጉን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። ባለፈው ወር፣ በሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ባንድ ቤት ውስጥ ተደብቀው የነበሩና ሕጻናትን ጨምሮ ከአሰሳ ያመለጡ 32 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ፖሊስ እያፈላለገ መኾኑን ገልጦ ነበር። ፖሊስ ዛሬ የታደጋቸው ፍልሰተኞች ጉዳይ፣ በመጋቢት ከተሠወሩት ጋር ይገናኝ ወይም አይገናኝ ለጊዜው አልተረጋገጠም ተብሏል። ባለፈው ጥር ወር በተመሳሳይ፣ ፖሊስ 26 ሕጋዊ ሰነድ ያልያዙ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች እርቃናቸውን ቤት ተዘግቶባቸው ማግኘቱ አይዘነጋም።