- ፌደራል ፖሊስ ለሶስተኛ ግዜ አክቲቪስቱን ማግኘት አልቻልኩም ብሏል፣ ዳኞች በበከላቸው ለፍትህ ስርዐቱ ያለውን ንቀት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል
(መሠረት ሚድያ)- ስዩም ተሾመ የተባለው አክቲቪስት የአቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና የአቶ ክርስቲያን ታደለን የክስ ሂደት አስመልክቶ በችሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ ግለሰቡን ሥነ-ሥርዓት እንዲያሲዘው መጠየቃቸውን አስመልክቶ በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።
ጉዳዩን እየተመለከተው የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር ወንጀል ችሎት አክቲቪስቱ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ስዩም ተሾመ የተባለውን ግለሰብ በዛሬው እለትም ለሦስተኛ ጊዜ የፌደራል ፖሊስ ግለሰቡን አላገኘሁትም በሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የችሎቱ ዳኞች በበኩላቸው “የፌደራል ፖሊስ ግለሰቡን ለደህንነቱ ሲባል እጀባ እያደረገለት እንደሆነ ይታወቃል።ነገር ግን ፍርድ ቤቱ እንዲያቀርበው ትዕዛዝ ሲደርሰው አላገኘሁትም የሚል ምላሽ መስጠቱ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ግለሰቡ መሀል አዲስ አበባ ተቀምጦ የፍርድ ቤቶችን ዳኞች ስም ሲያጎድፍ እየዋለ ነው። ከችሎቱ አቅም በላይ ሆኗል። ስለዚህ የፍርድ ቤቱ የበላይ አመራሮች ጉዳዩን ለማስቆም አለመሞከራቸው ያሳዝናል” ብለው በዛሬው ችሎት ላይ እንደተናገሩ የመሠረት ሚድያ ምንጮች ጠቁመዋል።
“አሁንም ግለሰቡ በፖሊስ ተይዞ ካልቀረበ እና የዳኞችን ስም የሚያጎድፍ ከሆነ ስራችንን ለማቆም እንገደዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።
አቤቱታውን ያቀረቡት አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በበኩላቸው “የዓቃቢ ሕግ ምስክሮች ለደኅንነታቸው ሲባል የስም ዝርዝራቸው እንዳይደርሰን ተከልክለን እያለ በዓቃቢ ሕግ አቶ ኢዮሲያድ አበጀ በኩል ለአቶ ስዩም ተሾመ ተሰጥቶት በማሕበራዊ ሚዲያ ማን እንደ ሚመሰክርብን ነግሮናል። ፍርድ ቤቱ የሚቀጣንንም ቅጣት ከወዲሁ ግለሰቡ እየነገረን ነው። እኛ በሕግ ቁጥጥር ስር እያለን ይሄ ሁሉ ዘመቻ ሲፈፀምብን ፍርድ ቤቱ ለምን ማስቆም አልቻለም?” ሲሉ አቤት ብለዋል።
ችሎቱ በበኩሉ “አሁን ጉዳዩ ከእናንተ ወጥቶ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ሆኗል። ከዚህ ችሎትም አልፎ አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚመለከት እየሆነ ነው። ለፌደራል ፖሊስ ደጋግመን መፃፋችንን ታውቃላችሁ። ማቅረብ የሚችለው ፖሊስ ነው። ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ካልፈፀመ የፍትሕ ሥርዓቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ይጠቁማል። ለጊዜው ይሄ ችሎት ማለት የሚችለው ይህንን ብቻ ነው” ሲሉ ዳኞች በምሬት ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ለአራተኛ ጊዜ ስዩም ተሾመን አስገድዶ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ችሎቱ ለሚያዚያ 30 ቀን 2017 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።