ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ሰራዊት አመራሮች “በዘረፋ እና በሰዎች ንግድ ላይ ተሳትፈዋል

አቶ ጌታቸው ረዳ ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ሰራዊት አመራሮች “በዘረፋ እና በሰዎች ንግድ ላይ ተሳትፈዋል” ሲሉ ወነጀሉ

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች “በወርቅ ቁፋሮ እና ንግድ”፣ “የመንግስት ገንዘብ በመዝረፍ” እንዲሁም ”በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል” ሲሉ ወነጀሉ።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በስም ጠቅሰው የወነጀሏቸው ሶስቱ አመራሮች፤ ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሃይለ፣ ብርጋዴር ጀነራል ሃይለስላሴ ግርማይ እና ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ ናቸው።

ትላንት ሰኞ ግንቦት 4፤ 2017 ምሽት በፋና ቴሌቪዥን የተላለፈው የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ክፍል አንድ ቃለ መጠይቅ፤ ስለ እርሳቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አጀማመር፣ በትግራይ ክልል ስለ ተካሄደው ጦርነት፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች እና የትግራይ ሰራዊት አዛዦች “ፈጽመዋቸዋል” ስላሏቸው ወንጀሎች የዘረዘሩበት ነበር።

አቶ ጌታቸው ተፈጽመዋል ካሏቸው ወንጀሎች ቅድሚያውን የሰጡት ለወርቅ ንግድ ነው። በትግራይ ክልል በህገወጥ መንገድ የሚካሄደው የወርቅ ንግድ የተጀመረው፤ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ከተፈራረሙ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. በኋላ የሚመስለው በርካታ ሰው እንዳለ አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ አንስተዋል።

ሆኖም በክልሉ ህገወጥ የወርቅ ቁፋሮም ሆነ ንግድ የተጀመረው፤ የትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ጭምር እንደሆነ የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ይፋ አድርገዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15872/