ክልል ጠቋሚ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች በአዲስ ሊተኩ መሆኑ ተጠቆመ

  • የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሥርዓቱን ለመቀየር ጥናት እያካሄድኩ ነው ብሏል

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ክልል ጠቋሚ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎችን በአገራዊ (ኢት – ET) ለመተካት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታወቀ።

ይህ የተገለጸው ሚኒስቴሩ ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ከተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ጋር፣ “የመሀሉ ዘመን” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ አገራዊ ሰነድ ላይ ውይይት ሲደረግ ነው።

የሪፖርተር ምንጮች በውይይቱ ወቅት የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ክልል ጠቋሚ የሆኑ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ሊቀየሩ መሆናቸውን፣ አገራዊ በሆነ ወጥ መለያ እንደሚተኩ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

የሰሌዳ አሰጣጥ ሥርዓቱን መቀየር አስፈላጊ ያደረገውም፣ የመጡበትን ክልል የሚጠቁም ሰሌዳ ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ ለሽብርና ለወገንተናዊ አሠራር ተጋላጭ እያደረገ መሆኑን በመሆኑ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ገልጸዋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ ክልሎች በራሳቸው መጠሪያ ሰሌዳ መሰየም መብታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይሁንና ይህንን እንደ መብት ማረጋገጫ ማሳያ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ፣ ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን እንደሚያስፈልግ ማብራራታቸውን ጠቅሰዋል።

ጉዳዮን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ አብዲሳ ያደታ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባይጀመርም፣ የሰሌዳ አሰጣጥ ሥርዓቱን መቀየር በተመለከተ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የጥናቱን ዝርዝር የትኩረት አቅጣጫዎችን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

‹‹በጥናት ሒደት ላይ ነው ያለነው፣ ጉዳዩን በተመለከተ በሕግ ኃላፊነት የተሰጠው ለሚኒስቴሩ ስለሆነ፣ የሰሌዳ አሰጣጥ ሥርዓታችንን ፈትሸን ጊዜው በሚፈልገው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል መሥሪያ ቤቱ ጥናት እያካሄደ ነው፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በተደረገው ውይይት የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ በበኩላቸው፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ራሳቸውን በማደራጀትና በማሳደግ፣ አገራዊ ዕድገቱን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል።