ኢትዮጵያ የመንግስት መፍረስ እንዳያጋጥማት ያሰጋል

ኢትዮጵያ፣ የሰላም ማግስት ሥጋት ምድር

ኢትዮጵያ ዛሬ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ ጋዜጠኞች፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተቺዎች፣ አቀንቃኞች፣ ባለሐብቶችና ሌሎች ዜጎችም በጠራራ ፀሐይ የሚታገቱ፣ የሚደበደቡ፣ የሚዘረፉባት፣ ፖለቲከኞች፣ምሑራን፣ጋዜጠኞች፣የኃይማኖት መሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ ጎሳና ኃይማኖት እየመረጡ እርስበርስ የሚካሰሱ፣የሚወዛገቡባት ሐገር ናት።

ከሺራሮ ጫፍ እስከ ደብረሲና ዋሻ አፍ፣ የሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያን ያነደደዉ ጦርነት ቆሟል።የዋንኞቹ ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ገቢር እያደረጉ ነዉ።እዉቁ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌዉ የስምምነት ሒደት፣ የእስካሁን ዉጤቱን

«የዘገየ ግን ጥሩ » ይሉታል

«አሁንም ዘግይቶም ቢሆን ነገሮችን በዉይይት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እሰዬዉ የሚያስብሉ ናቸዉ።ጥሩ ናቸዉ።»

የኢሕዴን መስራችና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ ደግሞ አስደሳች።

«በተጠናቀቁበት መልኩ መካሔዱ ደስ የሚያሰኝ ነኝ።»

ግን ኢትዮጵያ ሰላም ነች? ጥሩዉ ሒደት፤ አስደሳቹ ዉጤት መነሻ፣ የጥቅል ኢትዮጵያ ምስቅልቅል ማጣቃሻ፣ መፍትሔዉ መድረሻችን ነዉ።ከሁለቱ እንግዶቻችን ጋር ላፍታ አብረን እንቆይ።

ከብዙዎቹ የአረብ-እስራኤሎች ጦርነቶች አንዱ በቆመ ማግስት የያኔዉ የግብፅ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስርና የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ሊዮኔድ ብሬዥኔቭ ሲወያዩ— ናስር ለብሬዥኔቭ «የቀረበዉን የሰላም  ሐሳብ ልቀበል ነዉ» አሏቸዉ አለ የሁለቱን መሪዎች ዉይይት ይከታተል የነበረዉ እዉቁ የግብፅ ጋዜጠኛ መሐመድ ሐይከል።

ብሬዥኔቭ ደንገጥ፣ጣደፍ ግን ፈገግ ብለዉ «የአሜሪካ ባንዲራ ያለበትን?» ጠየቁ።«አዎ» መለሱ ናስር «የምቀበለዉም የአሜሪካ ባንዲራ ስላለበት ነዉ»—-

የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትና ያኔ መቀሌ ላይ የከተቱት የሕወሓት መሪዎች በየሰበብ አስባቡ ሲናጩ፣ ጠብ፣ሽኩቻ፣ ፍትጊያቸቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ያልመከረ፣ያልሞከረ፣ያላስጠናቀቀ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ፣ተንታኝና ጋዜጠኛ ከነበረ-እሱ አንድም የሁለቱ ወገኖች አካል- አባልና ደጋፊ-ሁለትም  ከጦርነቱ ለማትረፍ ያለመ ከነበረ።

በዉጊያዉ መሐል ተፋላሚዎች ዉጊያዉን አቁመዉ እንዲራደሩ መንግስታት፣የዉጪም-የዉስጥም ታዛቢዎች፣ መገናኛ ዘዴዎችምና የመብት ተሟጋቾች  ሲጎተጉቱ ነበር።

የታንክ፣መድፍ፣ድሮን ብዛትን እንጂ እሳት አረሩን በቅርብ የማያዉቁት የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎች፣ የአሜሪካና የአዉሮጳ አጫፋሪዎቻቸዉ ና ተከፋዮቻቸዉ ለየጥሪ-ጥያቄዉ የሰጡት መልስ የዚሕ ወይም የዚያ ወገን አባል፣ ደጋፊ የሚል ወቀሳ፣ ስድብ ዉግዘት ነበር።አቶ ልደቱ ያስታዉሳሉ።

«የኢትዮጵያ ሕልዉና ተቆርቋሪ የሚል አንድ ስብስብ ፈጥረን ነበር።ጦርነቱ በጣም አስቀያሚ እንደሆነ ሕዝብ ጨራሽ እየሆነ እንደሚሄድ እርግጠኞች ስለነበርንና ይኸ ጉዳይ በሰላም መፈታት አለበት የሚል ገና ከመጀመሪያዉ ዙር ጦርነት ላይ ነዉ ሐሳቡን ያነሳነዉ።»

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት  አንድ የጀርመን መፅሔት ስለዉጊያዉ ምክንያትና ሒደት ያተተበትን መጣጥፉን «ሁለት መላጦች ባንድ ሰባራ ሙሽጥ ይጣላሉ» የሚል ካርቱን ለጥፎበት ነበርት።የመጣጥፉ ማጠቃለያ ደግሞ «ሁለቱም ወይም ከሁለት አንዳቸዉ መንጋጋቸዉ ሲወልቅ» ዉጊያዉን ያቆማሉ» የሚል መዘባበቻ ነበር።

በርግጥ አላበለም።ዘንድሮ በሃያኛ ዓመቱ የአንዳቸዉ መንጋጋ በመንገጫገጩ ይሁን ብሬዥኔቭ እንዳሉት «የአሜሪካ ባንዲራ ያለበት ሐሳብ ሲመጣ» አንዱ ሌላዉን ለማጥፋት መቶ ሺዎችን ያረገፉት ጠላቶች ስምምነቱን ፈረሙ።ዉጊያዉን አቆሙ።እስካሁን ገቢራዊ አደረጉም።

ስምምነቱን ገቢር ማድረጉ ብዙ ቢቀርም የእስካሁን ሒደቱ ግን አቶ ያሬድ እንዳሉት አስደሳች ነዉ።ግን ጥርጣሬና ቅሬታም አሳድሯል።

«የኤርትራ አደጋ ሊቀንስ ችሏል።በዚያ ደስተኛ ነኝ።ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ አልቻለም።አሁንም ኢሮብ አካባቢ፣ ሁመራ አካባቢ የኤርትራ ኃይሎች እንዳሉ ይነገራል—–የወልቃይት ጉዳይ፣የሁመራ ሁዳይ፣የራያ ጉዳይ—–»

አቶ ልደቱ ሁለት ነገር ያነሳሉ።ስምምነቱ ከተፈራራሚዎቹ ዉጪ በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖችን ማግለሉ-አንድ እና ገቢራዊነቱ ግልፅ አለመሆኑን።

የተስማሙት፣የሁለቱ ኃይላት መሪዎች ናቸዉ።በጦርነቱ ወቅት ተፈፀመ ተብሎ ለሚታመነዉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂ የሚባሉት ግን በጦርነቱ የተካፈሉ በሙሉ ናቸዉ።ይሕም ተጨማሪ ቅሬታ አሳድሯል።

የሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት ከጥርጣሬ፣ቅሬታዉ ጋርም ቢሆን የፈጠረዉ ደስታ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተደጋጋሚ፤ ደቡብ ኢዮጵጵያ አልፎ-አልፎ በሚደረገዉ ጎሳ ለበስ ጥቃትና ግጭት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የተቀሰቀሱ ያስተዳደር ጥያቄዎችና ጥያቄዎቹን ለመደፍለቅ በሚደረገዉ ግብግብ ተጣፍቶ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ በዜሮ ዉጤት ማሳረጉ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።

ኢትዮጵያ ዛሬ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ ጋዜጠኞች፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተቺዎች፣ አቀንቃኞች፣ ባለሐብቶችና ሌሎች ዜጎችም በጠራራ ፀሐይ የሚታገቱ፣የሚደበደቡ፣የሚዘረፉባት፣ፖለቲከኞች፣ምሑራን፣ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ ጎሳና ኃይማኖት እየመረጡ እርስበርስ የሚካሰሱ፣የሚወዛገቡባት በአቶ ያሬድ አገላለፅ «ሥርዓተ አልበኝነት የተንሰራፋባት» ሐገር ናት።

አቶ ልደቱ ደግሞ ሐገሪቱ ከመክሸፍም አልፋ የመንግስት መፍረስ እንዳያጋጥማት ያሰጋል ባይናቸዉ።መፍትሔ አለዉ ይሆን? አቶ ልደቱ «አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ ድርድር» ይላሉ።

«ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ያለዉ ችግር በገዢዉ ፓርቲ ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም።ወይም በተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች ድርድር የሚፈታ ዓይደለም።ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሔ ነዉ የሚያስፈልገዉ።የመጀመሪያዉ ማመን ያለብን እሱ ነዉ።—–»

የፀጥታ ችግር፣ ከስፍራ ስፍራ የመንቀሳቀስ ሥጋት፤ የመስራት ፍርሐት፣ ሥራ የማግኘት ችግር፣ ሰርቶም የክፍያ ማነስ ችግር፣የኑሮ ዉድነት፣ የገንዘብ ግሽበት።ብዙና ዉስብስብ ነዉ።ግን የችግሩን ጥልቀትና ስፋት የሚያዉቅና ለጋራ መፍትሔ የሚጥር ፖለቲከኛ ካለ የማይቃለል አይደለም።ከሁለቱ ፖለቲከኞች ጋር ያደረግነዉን  ሙሉ ዉይይት ከነገ ጀምሮ ከማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎቻችን ማድመጥ ትችላላችሁ።