የገራገሩ ጀግና ጭንቀት – መስከረም አበራ

የገራገሩ ጀግና ጭንቀት
*******************
May be an image of 2 people, people sitting and indoorይሄን ሁለት ሶስት ቀን ጀነራል ተፈራ ማሞን ለመጠየቅ እስቤ ማን ቤቱን ያውቅ ይሆን እያልኩ ሳሰላስል ሰነበትኩ፡፡ የልቤን ማን እንደነገራት ቁምነገረኛዋ የየኔታ ቱብ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ትናንት ስልኬ ላይ ደወለችና “ጀነራሉን እንጠይቅ እንጅ” አለችኝ፡፡ “አሁን ከደቂቃዎች በፊት ከማን ጋር ልሂድና ልጠይቀው እያልኩ ነበር” አልኳት፡፡ “እኔ እወስድሻለሁ፣መቼ እንሂድ?” አለችኝ:: “ነገ ነዋ ምን መቼ አለው?” አልኩ፡፡ ‘ሳትነግሪን ለምን ሄድሽ?’ ሊል የሚችል ጓደኛ ጋር ሁሉ ደዋወልኩና የጀነራሉ ቤት ለመሄድ ተስማማን፡፡ ዛሬ ጉዞ ወደ ጀግናው ጀነራል ቤት ሆነ፡፡ ቤት ስንደርስ ቆንጅየዋ ባለቤታቸው መነን በፈገግታ ተቀብላ የግቢ በር ከፍታ አስገባችን፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ጀግናችን አልጋ ላይ ነው! ሲያየኝ መነሳቱ እንደማይሆን እያወቀም ሳያስበው እንደመነሳት አለ፣የያዘው ደግሞ መልሶ ወደ አልጋው ሳበው፡፡ ፈጠን ብየ ተጠጋሁትና ሰላም አልኩት፡፡

አልጋ ላይ ተሰፍቶ ሳየው ደስ የማይል ስሜት ተሰማኝ፡፡ጀግና እንዲህ አያምርበትም! እሱ አብረውኝ የመጡ ሰዎችን ሰላም ሲል እኔ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ በሞባይል ሲያዋጋ ያየሁት ፎቶው ፊቴ ድቅን አለ፡፡ ውለታ የማልረሳ ሰው ነኝ – ወርቅ ያበደረ ባለውለታ ጠጠር ሲመለሰለትም የሚቆጨኝ እልኸኛ! “አይዞህ ደህና ነህ” አልኩት ሳላውቀው፡፡ “ምንም አልል፣መንቀሳቀስ ችግር ሆነ እንጅ” አለኝ ፈገግ እያለ፡፡ አስከትሎም “ልጅሽ አደገ፤ጥለሽው እየታሰርሽ አንገላታሽው፤ መቼም ያኔ አራስ ሆነሽ ስትታሰሪ በጣም ነው ያዘንኩት ምን ማድረግ ያለመቻል ያናድዳል” አለኝ፡፡ “አንተማ ብዙ አድርገሃል፣ብዙ ማድረግ የምትችል መመኪያችን ነህ! ጤናህን እንዴት ነህ ግን” አልኩት፡፡ አብረውኝ የመጡ ሰዎች የእኔን እና የእሱን ምልልስ ፀጥ ብለው ያዳምጣሉ፡፡ “ያው ጥይት የመታኝ ብዙ ቦታ አለ፣ችላ ብየው ኖሬ አሁን ነርቬን እየነካ አላራምድ አለኝ፣ልራመድ ካልኩ ህመሙ አያድርስ ነው፡፡ የሚከታተሉኝ ሃኪሞች ከፍተኛ ህክምና ማግኘት ስላለብኝ ውጭ ሃገር ሄጄ እንድታከም ነው የመከሩኝ፡፡ ሆኖም መንግስት አልፈቀደምና ከህመሜ ጋር ቁጭ ብያለሁ” አለኝ፡፡

“ለምንድን ነው ግን የከለከሉህ?” አልኩኝ “ማን ይነግርሻል? ሁሉን ከጨረስን በኋላ ነው ጉዞው ተከልክሏል የሚል ነገር በእስክርቢቶ ፓስፖርቴ ላይ ፅፈው የመለሱኝ፤ በሚዲያ በምናገረው ነገር መሪዎቹ ደስተኛ እንዳልሆኑ ነው ከአንዳንድ ለእነሱ ከቀረቡ ምንጮች የሰማሁት” አለኝ፡፡ “እንኳን ልክ ያልመሰለህን ነገር ተናገርክ፣እንኳን ከሃቅ ጋር ወገንክ፣ ሃቅህ ያድንሃል፣ ፈጣሪ አለ፣ህዝብም ከጎንህ ነው” አልኩት፡፡ “አይ የእኔ ነገር እምብዛም አያሳስበኝም፤ ይህ መከረኛ ህዝብ አሁንም በዝርግ ተገኝቶ ለሶስተኛ ጊዜ እንዳያልቅ ነው የምፈራው፤ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ ነው የሚያስፈራኝ፤ ህዝቡ በተደቀነበት አደጋ ልክ በሁለንተናዊ መንገድ ተደራጅቶ ራሱን ለማዳን እንዲታገል በማለቴ ነው እንግዲህ የመንግስት ቅሬታ፡፡ እንዲህ አልጋላይ ሆኜም የህዝቡ እጣ ፋንታ በእጅጉ ያሳስበኛል፤የሚያሳዝን ህዝብ ነው፡፡ ለህዝብ እኮ ዋናው መሪ ነው፡፡ ታላቁ ህዝባችን መሪ አጥቶ ነው ሁሌ በአደጋ ውስጥ የሚኖረው” ብሎ እንደ መተከዝ ሲል፡፡ “አይ ህዝቡ ደግሞ ስለ አንተ ነው የሚጨነቀው፤አንተ አሁን ለራስህ ነው ማሰብ ያለብህ፤ህክምናህን በምታገኝበት መንገድ ላየ ነው አሁን መተኮር ያለበት” አልኩኝ፡፡

ጄነራሉ ግን ተመልሶ ስለ አማራ ህዝብ እጣ ፋንታ መናገር ጀመረ፤ልንጠይቀው የመጣን ሁላችንም ተከትለነው በጥያቄ እናጣድፈው ገባን፡፡ ለእኛ የጥያቄ ናዳ በሚሰጠው መልስ ስለ ህዝባችን ብዙ ብዙ አወጋን፡፡ ጄነራል ተፈራ ከገመትኩት በላይ ገራገር፣ግልፅ እና ፈገግታ የማይለየው ቀለል ያለ ሰው ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የሄድን ወዳጀቼ ሁሉ እንደ ጓደኛ ነው ያወጋነው፡፡

ከሁለት ሰዓት በላይ በቤቱ ቆየን፤ በዚህ ሁሉ መሃል ለሁላችንም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሲሞክር አካላዊ እንቅስቃሴውን ሁሉ አጥብቃ የምትከታተለው፣ በራስጌው በኩል የተቀመጠችው ባለቤቱ መነን በተንቀሳቀሰበት አቅጣጫ እየተከተለች የከበበውን ትራስ ታስደግፈዋለች፣”ተው ተፌ እንደሱ አትሁን” እያለች ታስጠነቅቃለች፡፡ የክትትሏ፣የመጠንቀቋ ነገር የሚገርም ነው፡፡ ቆይታችንን ጨርሰን ስንወጣ ሁላችንም መነንን አመሰግነን ጀግናችንን ተሰናብተን አልጋው ላይ ተኝቶ በልቡ የወጣበት ህዝብ እጣ ፋታ የሚያባዝነውን ጀግናችንን ከህመሙ ጋር ትተነው ወጣን፡፡ ይህ ሰው የሁላችንም ጉዳይ መሆን አለበት፣ይታከም ዘንድ አብዝተን ልንጮህለት ይገባል፡፡ህዝብ በተጨነቀ ሰዓት የደረሰበትን ተደራራቢና ተደጋጋሚ በደል ሳይቆጥር ሊሞት የመጣልን ጀግና አንድ ክፍል ውስጥ ከህመሙ ጋር ተዘግቶ ሲቀመጥ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ልንል ከቶ አይገባም!