ኢትዮጵያ ኢንሳይደር – የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ከክልሉ ውጪ ባሉ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት እንዲመረጡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ወሰነ። ውሳኔውን ያስተላለፈው ችሎቱ፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የምርጫ ሂደት ከዚህ ቀደም ላለፉት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ሲደረግ በነበረው አኳኋን እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን የተመለከተው፤ “የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ከክልላቸው ውጪ በሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሊመረጡ ይችላሉ” በማለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይግባኝ በማለቱ ነበር። የምርጫ ቦርድን የቅሬታ ነጥቦች እና የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤን ምላሽ በጽሁፍ እና በቃል ክርክር የተመለከተው ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ሐሙስ ግንቦት 19 ቀጠሮ ይዞ ነበር።
ችሎቱ ባደረገው ምርመራም የግራ ቀኙ ክርክር መሠረት ያደረገባቸውን ጭብጦች ተመልክቷል። የመጀመርያው ጭብጥ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተያዘው ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን አለው ወይስ የለውም የሚል ነው። በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ “ቦርዱ በሚወስናቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ቅር የተሰኘ አካል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል” ተብሎ መደንገጉን የጠቀሰው ችሎቱ፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን አለው ሲል አስቀምጧል።
ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላትን የምርጫ ሂደት በተመለከተ የሐረሪ ሕገ መንግስት የሚደነግገው ከፌደራል ሕገ መንግስት ጋር የሚቃረን ስለሆነ፤ “ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ነው እንጂ ፍርድ ቤቱ ሊወስን አይገባም” የሚል መከራከሪያ በተጨማሪነት አቅርቦ ነበር። ለዚህ ምላሽ የሰጠው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፤ ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ሀሳቦች ፍርድ ቤት የመወሰን ስልጣን አለው ሲል ወስኗል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ ፍርድ ቤት የቀረቡትን አቤቱታዎች ተመልክቶ ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ካመነ ብቻ ለሚመለከተው አካል እንደሚያስተላልፈው አመልክቷል። በመሆኑም ምርጫ ቦርድ በዚህ ረገድ ያቀረባቸው መከራከሪያዎች “አግባብነት የላቸውም” ሲል ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ምርጫ ቦርድ “የሐረሪ ክልል ሕገመንግስት ከፌደራል ህገመንግስት ጋር የሚጋጭ ነው” በማለት የብሔራዊ ጉባኤው አባላት ከክልሉ ውጪ ሊመረጡ አይገባም ያለበትን አግባብም ፍርድ ቤቱ መርምሯል። ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለዚህ ጉዳይ በሰጠው ውሳኔም፤ ሁለቱ ህገመንግስቶች እንደሚቃረኑ ስልጣን ባለው አካል ተረጋግጦ እስካልተወሰነ ድረስ የሐረሪ ክልል ህገመንግስት ህጋዊ ሆኖ ይቆያል ብሏል። ምርጫ ቦርድም በራሱ ፈቃድ የክልሉ ሕገ መንግስት ከፌደራል ሕገ መንግስት ጋር ይቃረናል ማለቱ አግባብ አይደለም ሲልም ተችቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራሉ ሕገ መንግስት፤ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ብሔረሰቦች ማንነታቸው፣ ባህላቸው እና ቋንቋቸው እንዳይጠፋ የተለያዩ ጥበቃዎችን እንደሚያስቀምጥ ፍርድ ቤቱ አንስቷል። “የሐረሪ ብሔረሰብም የዚህ ጥበቃ ተጠቃሚ ነው” ያለው ችሎቱ፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላትም ከክልሉ ውጪ በሚገኙ ነዋሪዎች እንዲመረጡ የተደረገው በዚህ ጥበቃ ስር ነው ሲል አትቷል።
የምርጫ ቦርድ መከራከሪያዎችን በዚህ መልኩ ውድቅ ያደረገው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የመመረጥ መብትን በተመለከተ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የወሰነው ውሳኔ “ትክክለኛ ነው” ሲል አጽንቶታል። በዚህም መሰረት “የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ከክልሉ ውጪ ባሉ የብሔረሰቡ ተወላጆች መመረጥ ይችላሉ” ሲል ውሳኔ አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)