የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ፣ ከትላንት ምሽት ጀምሮ ባንዳንድ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ጸጥታ ኃይሎች መሠማራታቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሠምታለች። በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ የሙከጡሪ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች፣ የክልሉ ፖሊስና ሚሊሺያ ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ መግባታቸውን ምንጮች አስረድተዋል። በፍቼ አጠቃላይ ሆስፒታልም፣ የጸጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ መኖሩን ዋዜማ ተረድታለች። ምዕራብ ጉጂ ዞን ሃምበላ ወረዳ የአምስት ጤና ጣቢያዎች የጤና ባለሙያዎች፣ በጸጥታ ኃይሎች ጫና አድማ ማድረግ እንዳልቻሉ ገልጸዋል። ባንዳንድ ሆስፒታሎች የጤና ባለሙያዎች አድማ እንዳያደርጉ፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ማስፈራሪያ ሲፈጽሙ እንደነበርም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎች የጤና ባለሙያዎች ከዛሬ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን አስታውቋል። የጎንደርና ጎባ ሆስፒታሎች አስተዳደሮች፣ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራቸው ባስቸኳይ ካልተመለሱ ርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል። ማኅበሩ፣ በአድማው ወቅት የድንገተኛ፣ የጽኑ ሕሙማን፣ የጨቅላ ሕጻናትና የማዋለጃ ክፍሎች ብቻ አገልግሎት እንደሚሠጡ ገልጧል። የጤና ባለሙያዎች እየታሠሩና ዛቻ እየደረሰባቸው እንደሚገኙ የገለጠው ማኅበሩ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ባስቸኳይና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል። የጤና ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ በቀጣዩ ዓመት ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ በጀት ለመመደብ ዝግጅቶች እየተደረጉ መኾኑን ትናንት ምሽት ለብሄራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።
በተያያዘ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ መንግሥት የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮናታን ዳኘውንና ከሥራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ የታሠሩ ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን ከእስር እንዲፈታ ጠይቋል። አምነስቲ፣ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ ነጻነትን እንዲያከበርና የጤና ባለሙያዎችን መብት መጣስ እንዲያቆም ጭምር አሳስቧል።