ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት የኢጣሊያዊቷ ጋዜጠኛ ጥያቄ እና የካስትሮ ወሽመጥ ቆራጭ መልስ!

≪የኢጣሊያዊቷ ጋዜጠኛ ጥያቄ እና የካስትሮ ወሽመጥ ቆራጭ መልስ!
የካቲት 26 1970  ብሔራዊ ድላችን !!!

የመስፋፋት ፖሊሲ አራማጁ የሶማሊያ መንግስት በዕብሪተኛው መሪ «በዚያድ ባሬ» ትዕዛዝ የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ ገባ። ምዕራባዊያኑ ያስታጠቁት ዘመናዊ መሳሪያው፣ ለአመታት የተዘጋጀበት ጠንካራ የጦር ኃይል ሀገራችን ከነበረችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር እጅግ የማይቋቋሙት ጠላት ቢሆንም፣ የፈለገ ቁርሾ ውስጥ ቢገባና እርስ በእርስ ሲባላ ቢቆይም ለባዕድ ወራሪ አንድነቱን ጠግኖ ለሀገሩ መውደቅ የደሙ መለያ የሆነው አበሻ ከያለበት ተጠራርቶ በሀገር ላይ ያንጃበበውን የወረራ ጥቃት ለመቀልበስ ወደፊት አለ።

ምንም አይነት የተደራጀ የጦር ኃይል በጊዜው ያልነበራት ኢትዮጵያ በወቅቱ ያቀረበችውን የእናት ሀገር ጥሪ በመቀበል በአጭር ጊዜ 300 ሺህ የሚሊሺያ ሰራዊት ለስልጠና ታጠቅ ጦር ሰፈር ገባ። ከነበረው አጭርና አንገብጋቢ ጊዜ ከሶስት ወር ያልዘለለ ስልጠና የወሰደው ህዝባዊ ጦር ግዛታችንን አልፎ የገባውን ወራሪውን ጦር ሊጠራርግ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል ዘመተ።

አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ አንድ ጊዜ ግሩም አርጎ የግማሽ ሰአት ዶክመንተሪ ፊልም የሰራለት የእነ_ጄኔራል ፋንታ በላይ እና የእነ ጄኔራል ለገሰ ተፈራ የአየር ኃይል ምርጥ ብቃት ምስጋና ይግባውና ከሰማይ የቦንብ ውርጅብኝ በተደጋጋሚ እያዘነበ የምድሩን ውጊያ አቀለለው። የሶማሊያ ጦር በአየር ኃይል ፓይለቶቻችን ከላይ እንደእባብ እየተቀጠቀጠ ፍርክርክሱ ሲወጣ፣ እግረኛው ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የዚያድ ባሬን ጥጋበኛ ጦር አስተነፈሰው። ካራማራ ላይ በተካሄደው ከባድ ውጊያ ከፍተኛ መስዕዋትነት ተከፍሎ የተወረረው የኢትዮጵያ መሬቶች ከጠላት መዳፍ ተላቀቀ። ሶማሊያም የእፍረት ካባዋን ተከናንባና ሁለተኛ አይለምደኝም ብላ በመጣችበት እግሯ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

ሀገራችን በወቅቱ የሶሻሊስት አይዲዎሎጂ የምትከተል ሀገር ስለነበረች በተወሰነ መልኩ የሶሻሊስት ሀገሮች የወታደራዊ ድጋፍና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችም በቀጥታ ውጊያ ቢያግዟትም «ድሉ ከእነሱ ተጽህኖ የመጣ ነው!» የሚያስብል ግን አልነበረም። ግን ሁሌም የማይተኙላት ምዕራባዊያኑ የመገናኛ ብዙሃን እንደተለመደው «ኢትዮጵያዊያን ይሄን ጦርነት ያሸነፉት በኩባ ወታደሮች እገዛ እንጂ፣ በራሳቸው የውጊያ ብቃት አይደለም!» ብለው ማራገባቸው አልቀረም። በእርግጥ የኩባ ወታደሮች በዚያ ክፉ ዘመን ከእኛ ጋር ተሰልፈው በመወጋት ውለታ ውለዋልም፣ ወደ 110 የሚደርሱ ወታደሮችም በውጊያው ተሰውተዋል። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ ያለው የመታሰቢያ ሀውልትም የቆመው ለእነዚህ የኩባ ወታደሮች ክብር ማስታወሻ ተብሎ ነው። ግን ድሉ ወራሪን ቀጥቅጦ ልክ በማስገባት ከሚታወቁት ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ የመነጨ ነው።

ታዲያላችሁ አንድ ወቅት ላይ ኢጣሊያዊት ጋዜጠኛ የኩባውን መሪ ፊደል ካስትሮ አግኝታ በዚህ ጦርነት ዙሪያ አንድ ጥያቄ አነሳችላቸው…..

ኢጣሊያዊቷ ጋዜጠኛ…….≪ በሱማሊያና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው ጦርነት ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር አጋር ሆና ተሰልፋ ነበር!≫

ፊደል ካስትሮ……≪ እንደማንኛውም ወዳጅና ወንድም ሀገር በተወሰነ መልኩ አግዘናቸዋል!≫

ኢጣሊያዊቷ ጋዜጠኛ……≪ በተወሰነ መልኩ ሳይሆን ለድሉ መገኘት የኩባ ወታደሮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያዊያን ግን ጦርነቱን ያሸነፍነው በእኛ ጀግንነት ነው ይላሉ፣ እውነት እርስዎም በኢትዮጵያዊያን ጀግንነት የመጣ ድል ነው ብለው ያምናሉ!≫

ፊደል ካስትሮ……≪ ጀግንነት በእርግጥ ለኢትዮጵያዊያን ብርቅ ነገር ነው ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ናቸው? ወይስ ጀግኖች አይደሉም? የሚለውን ምስክርነት እኔ ልሰጥሽ ከምችለው በላይ የሚሰጡሽን ሰዎች ለምን አትጠይቂያቸውም?≫

ኢጣሊያዊቷ ጋዜጠኛ…..≪ እነማናቸው እነሱ?≫

ፊደል ካስትሮ…….≪ የራስሽ አያቶች ናቸዋ!!!≫