በአቶ ጌታቸው የሚመራው ህወሓት ‘ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የሚባል አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም ነው

በአቶ ጌታቸው የሚመራው ህወሓት ‘ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የሚባል አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም ነው

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ከህወሓት የተከፈለው ቡድን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም በሂደት ላይ መሆኑን ከአመራሮቹ መካከል አንዱ ለቢቢሲ ገለፁ።

ይህ አዲስ በምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲ በሊብራል ዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ የሚከተል መሆኑን የተናገሩት አመራሩ “ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” በማለት ለመጠራት መወሰኑን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እኚህ የቀድሞ የህወሓት አመራር “ይህ ስም የፖለቲካ ፓርቲውን ለመመሥረት በእንቅስቃሴ ላይ ባሉ ሰዎች የተመረጠ እንጂ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ስላላገኘ ጉባዔ ሲካሄድ ሊቀየር ወይንም ሊሻሻል ይችላል” ብለዋል።

በሁለት ተከፍሎ እርስ በእርሱ ሲካሰስ የቆየው ህወሓት የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ ጉባዔ ማካሄድ ባለመቻሉ ከፓርቲነት ሊሰረዝ እንደሚችል ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመሰረዝ አደጋ የገጠመው በደብረፂዮን (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተደራድሮ የፕሪቶሪያ ስምምነትን እንደፈረመ ድርጅት እንደ አዲስ በቦርዱ መመዝገቡ ተገቢ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

የህወሓት መሰረዝ ስጋት የፈጠረባቸው በአቶ ጌታቸው የሚመራው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሳምንታት በፊት ባወጡት መግለጫ በደብረፂዮን (ዶ/ር) ለሚመራው ቡድን በጋራ ጉባዔ ለማካሄድ ጥሪ አቅርበው የነበረ ቢሆንም በጎ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይላሉ የቢቢሲ ምንጭ “የህወሓት ሕጋዊነት ስለሚያበቃ የህወሓት የፖለቲካ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚያስችለን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ተገድደናል” ያሉ ሲሆን የፓርቲው ሕገ ደንብ እና ፕሮግራሞቻችን አርቅቀው መጨረሳቸውን ተናግረዋል።

ምንጩ አክለውም የደጋፊዎቻቸውን ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይኹን አንጂ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ገና ስላላሟሉ እስካሁን ድረስ ለቦርዱ በይፋ ያቀረቡት ጥያቄ እንደሌለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ይህ ስብስብ ለምዝገባ እየሄደበት ያለውን ሂደት እንደሚያውቅ ምንጩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ በምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኘው ፓርቲ ክልላዊ ፓርቲ እንደሆነ የተናገሩት ግለሰቡ፣ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በግንቦት የመጀመሪያ ወር ላይ ቅድመ እውቅና እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እየመሠረቱ ካሉተ አንጋፋ ሰዎች መካከል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት እና የትዕምት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በየነ መክሩ እንዲሁም ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት እንደሚገኙበት ታውቋል።

አሁን ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ ያለው ፓርቲ በሌ/ጄነራል ታደሰ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአንድ ዓመት ጊዜ ካበቃ በኋላ ክልላዊ መንግሥትን ለመመሥረት በሚደረገው ምርጫ እንደሚሳተፍ ምንጫችን ገልፀዋል።

አዲስ የሚመሠረተው ትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅና ካገኘ በኋላ ከባለሀብቶች እስከ የቀን ሠራተኞች ድረስ በአባልነት እና በአመራርነት ተቀላቅለው ሊሳተፉበት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከፓርቲው መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እና ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የትምህርት ሚኒስትር አማካሪ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መሾማቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ እየተመሠረተ ያለው ፓርቲ ከብልጽግና ጋር የሚያገናኘው ነገር መኖሩን የጠየቃቸው ከመሥራቾቹ አንዱ የሆኑት ግለሰብ “ትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከብልጽግና ጋር ልክ እንደሌሎቹ በአገር ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተባብሮ ለመሥራት ይችላል እንጂ የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ገለልተኛ እና ነጻ ፓርቲ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

በ1967 ዓ.ም. በደደቢት በረሃ የተመሠረተው ህወሓት ከትግራይ ጦርነት በኋላ በገጠመው የአመራር ቀውስ ለሁለት ተከፍሎ እርስ በእርሱ ሲካሰስ ቆይቷል።

በእነደብረፂዮን የሚመራው ህወሓት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጉባዔ ቢያካሄድም የምርጫ ቦርድ ስላልተቀበለው ጉባዔውን እንደ አዲስ እንዲያካሄድ ተጠይቆ ነበር።

ህወሓት እንደ አዲስ አልመዘገብም በማለት የምርጫ ቦርድን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።

ህወሓት እንደ ፓርቲ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንደ ፓርቲ እውቅና የማያገኝ ከሆነ “መዘዙ የከፋ ነው” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው