የብልፅግናው አቃቢ ሕግ በቢሯቸው አስረው ሲያሰቃዩት የነበረው ግለሰብ ጉዳይ እያነጋገረ ነው

ተከሳሹ ወጣት በአቃቤ ህጉ በደረሰበት ድብደባ የጀርባ አጥንቱ መሰበሩን ገልፆ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲላክ ተማፀነ 

  • ፍርድ ቤት ተከሳሹ ዛሬውኑ ወደ ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ እንዲላክ እና ህክምና እንዲያገኝ አዟል 

(መሠረት ሚድያ)- ታሪኩ ተፈራ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት በአዲስ አበባ ከተማ ከግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን የሽብር ወንጀል ሊፈፅም ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን ክሱ ያስረዳል።

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው በዛሬው ዕለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሽብር ወንጀል ችሎት ቀርቦ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው “ለምርመራ በሚል ፖሊስ ለዓቃቢ ሕግ አሳልፎ በመስጠት ከአራት ወራት በላይ ናትናኤል ስንታየሁ በተባለ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ውስጥ ተዘግቶብኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈፀምብኝ ነው የቆየው” ሲል ዛሬ ለችሎቱ አስረድቷል።

ታሪኩ አክሎም “አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፅምብኝ የነበረውም እዚህ በግራ በኩል የቆመው ዓቃቢ ሕግ ናትናኤል ስንታየሁ ነው። በድብደባ ብዛት የጀርባ አጥንቴ ተሰብሯል፣ እንደምትመለከቱኝ ሰው ካልደገፈኝ መቆም አልችልም፣ ሽንቴን እንኳ መቆጣጠር አቅቶኝ ሰውነቴ ተበላሽቷል። እባካችሁ ከእገታ አስለቅቁኝ። ምርመራው አልቆ ክስ መስርቶብኛል። ከዚህ በኋላ ለምንድን ነው በቢሮው የሚያስቀምጠኝ። ዛሬውኑ ወደ ማረሚያ ቤት ላኩኝና ከሰው ጋር ልቀላቀል” ሲል ተናግሯል።

ችሎቱ በበኩሉ ግብረ አበሮቹ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ክስ ተመስርቶባቸው ቂሊንጦ የእስረኞች  ማቆያ ሲወርዱ ለምን ታሪኩ ተፈራን ነጥለው እንዳስቀሩት እና ሌሎቹ ተከሳሾች ከአራት ጊዜ በላይ በዚህ ችሎት ሲቀርቡ ለምን እሱን አላቀረባችሁትም የሚል ጥያቄ ያነሳ ቢሆንም “የጀርባ አጥንቱ ስለተጎዳ ሕክምና ለመውሰድ ነው ያቆየነው” ሲሉ ዓቃቢ ሕጉ አቶ ናትናኤል ስንታየሁ መመለሳቸውን የመሠረት ሚድያ ምንጮች ጠቁመዋል።

ፍርድ ቤቱም ታሪኩ ተፈራ ዛሬውኑ ወደ ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ እንዲሄድ እና አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኝ ሲል ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።