የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ቄስ ዶ/ር ጄሪ ፒሌይ፣ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው መግለጣቸውን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጥቃቱ እጅግ እንዳሳሰባቸው የጠቀሱት ዋና ጸሃፊው፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ንጹሃን በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶችን በእጅጉ ይኮንናል ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል። ዋና ጸሃፊው፣ በግጭት ውስጥ ተዋጊ ያልኾኑ ሰዎችን ከጥቃት በማያስጠብቅና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ባልተከተለ መልኩ የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች አሳሳቢ እንደኾኑ ተናግረዋል ተብሏል።
አገር ዓቀፍና ዓለማቀፍ ባለድርሻ አካላትም፣ ለግጭቶች ሁሉን ዓቀፍ ውይይትና ሰላማዊ መፍትሄን እንደ ብቸኛ መፍትሄ እንዲከተሉ ዋና ጸሃፊው መማጸናቸውን መግለጫው አውስቷል። https://www.oikoumene.org/news/wcc-condemns-drone-attack-in-ethiopia