የህክምና ባለሙያዎችን ድምፅ ያስተጋቡ አንድ ዶክተር ውሳኔ ተላለፈባቸው

የህክምና ባለሙያዎችን ድምፅ ያስተጋቡ አንድ ዶክተር ከድሬዳዋ ከተማ ተሰናብተው ገጠር ሄደው እንዲሰሩ ተወሰነባቸው

  • የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ድርጊቱን ተቃውመው ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል

(መሠረት ሚድያ)- በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ሳቢያን አጠቃላይ ሆስፒታል ሰራተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት እና ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች ያሰሙትን ድምፅ ያስተጋቡ አንድ ጠቅላላ ሐኪም የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው ገጠር ሄደው እንዲሰሩ እንደተወሰነባቸው ታወቀ።

መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና ሚያዝያ 9/2017 ዓ/ም በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ የተፃፈው ደብዳቤ ዶ/ር ሀብታሙ አለሙ የተባሉት እኚህ የጤና ባለሙያ ‘የሙያ ስነምግባርን የተፃረረ ድርጊት’ መፈፀማቸውን ጠቅሶ ጉዳዩ ባለመታረሙ አሁን ከሚሰሩበት የድሬዳዋው ሳቢያን ሆስፒታል ወደ ለገኦዳ ጉዱንፈታ ጤና ጣብያ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን ይገልፃል።

“የዛሬ ወር ገደማ ቋሚ ቅጥር ከሳቢያን ሆስፒታል ጋር ፈፅሜያለሁ። ይህ ሆኖ እያለ ከሰሞኑ እኛ የኢትዮጵያ የጤና ተቋማት ሰራተኞች ድምፅ እያሰማን መሆኑን ተከትሎ እኔም አንዳንድ ፅሁፎችን ስላወጣሁ ኢላማ ተደርጌያለሁ” ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ባሉት ቀናት ስልክ እየተደወለ በጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ዙርያ አስተያየት እንዳይሰጡ ማስፈራርያ ሲደርሳቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

“እኔ በበኩሌ ጉዳዩ የመኖር እና አለመኖር መሆኑን ጠቅሼ እንደማላቆም ነገሬያቸዋለሁ። የከተማው ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑትን ዶ/ር ፅጌረዳን ለማናገር ብሞክርም ያልተገባ ነገር ተናግረውኝ ስልክ ዘግተውብኛል” የሚሉት የጤና ባለሙያው ከዚያም እኚህ ሀላፊ ዶ/ር ሀብታሙ ወደሚሰሩበት ሆስፒታል በመደወል ከስራቸው እንዲታገዱ ማድረጋቸውን መስማታቸውን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ በቅርቡ ‘Hakim’ የተባለ የፌስቡክ ገፅ ላይ በርካቶች የተመለከቱት አንድ ፅሁፍ አጋርተው የነበረ ሲሆን እሱም “ስራዬ አድካሚ ቢሆንም፣ ደሞዜ ከ10,000ብር  በታች ቢሆንም፣ የአእምሮ እርካታ ይሰጠኛል። ሆኖም… እርካታ ቤት ኪራይ አይከፍልም። እርካታ በቀን 3 ጊዜ መብላት አያስችልም። እርካታ ልጆቼን ለማስተማር አያስችልም። እርካታ ልብስ እና ጫማ ለመቀየር አያስችልም። እርካታ ትዳር መመስረት አያስችልም። እርካታ ለታክሲ ወረፋ ከመጠበቅ አያድንም። ጥያቄያችን ለሁሉም ግልፅ የሆነ ነው። የሚገባንን እንኳን ባይሆን የሚያስፈልገን ይደረግልን። ትኩረት ለጤና ባለሞያዎች!” የሚል ነበር።

ዶ/ር ሀብታሙ ለመሠረት ሚድያ በሰጡት ቃል ተወልደው ባደጉበት የድሬዳዋ ከተማ እስካሁን እየሰሩ እንዲቆዩ የፈለጉበት ምክንያት በፅኑ ህመም አጋጥሟቸው የእለት ተእለት ክትትል የሚያስፈገልጋቸው የቤተሰብ አባል ስላላቸው በመሆኑ እና እሳቸውም ብቸኛ አስታማሚ መሆናቸውን አስረድተው ይህን የሚያሳይ የድል ጮራ ሆስፒታል ዶክመንት ለሚድያችን አሳይተዋል።

በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ላይ ለድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ቅሬታ እያስገቡ የሚገኙት የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

“የሞያ አጋራችን የሆኑት ዶ/ር ሀብታሙ አለሙ በሞያቸው የተመሰገኑ፣ ትሁት፣ ስራቸውን የሚወዱ እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ በታካሚ እና በስራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ ከዛም አልፎ ከስራቸው ውጪ በበርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎቻቸው የሚታወቁ ከተማችን ወደፊት ከሳቸው ብዙ  ምትጠብቅባቸው ወጣት ሀኪም ናቸው” ያሉት የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ስማቸውን ከማይገናኝ ነገር ጋር በማያያዝ፤ በማጠልሸት እና የሌላቸውን ስብዕና በመስጠት አግባብ ያልሆነ የውሸት ክስ በመደርደር በድሬዳዋ ከተማ ጤና ቢሮ የተሰጠውን ውሳኔ ኮንነዋል።

“የተሰነዘረባቸው ከእውነት የራቀ የሀሰት ክስ ትክክል እንዳልሆነ እኛ በቅርበት አብረናቸው የምንሰራ እና የምናውቃቸው የጤና ባለሞያዎች እና የሞያ አጋሮቻቸው በቂ ምስክሮች ነን” በማለት የቀረበበት ክስ እውነት እንኳ ቢሆን ቀድሞ ክስ ሊያቀርብበት እና የስነምግባር ግድፈት ተገኝቶበታል ብሎ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችለው እየሰራ የሚገኝበት ሆስፒታል እንጂ ባለሞያውን በቅርበት የማያውቀው አካል አይደለም ብለዋል።