የአብይ አሕመድ ዲፕሎማት ተገደሉ

በሱማሊያዋ ፑንትላንድ ራስ ገዝ የኢትዮጵያ ቆንስላ ውስጥ ተመድበው ይሠሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት ፋራህ አይዲድ ጃማ ከሱማሌላንድ ራስ ገዝ በቅርቡ በተነጠለችው “ኤስ ኤስ ካቱሜ” ግዛት ላስ አኖድ ከተማ ውስጥ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉን የሱማሊያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የግዛቲቷ ባለሥልጣናት፣ ግድያውን የፈጸሙት የአልሸባብ አባላት ሳይኾኑ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

በዲፕሎማቱ ሕልፈት ዙሪያ የግዛቲቱ ባለሥልጣናት ምርመራ እያደረጉ እንደኾነ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በዲፕሎማቱ ሕልፈት ዙሪያ በይፋ ያለው ነገር የለም።

የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ ከሶማሌላንድ መገንጠል እንፈልጋለን ያሉ የጎሳ ሚሊሻዎች ከደም አፋሳሽ ውጊያ በኋላ የመሠረቷትን “ኤስ ኤስ ካቱሜ” ግዛት፣ ባለፈው ሳምንት የፌደሬሽኑ አባል ግዛት አድርጎ መቀበሉን ማወጁ ይታወሳል።