በአባ ገብርኤል የስሕተት ‘ስብከት’ ላይ የቀረበ ሙሉ ትችት
(መምህር Arega Abate (ዶ/ር) እንደጻፈው)
አባ ገብርኤል ከውጭ ወደ ውስጥ ያስተጋቡትን ትችት አዘል፣ በስሕተት የተሞላውን ስብከታቸውን በተመለከተ ትናንት ማታ ከመምህር በረከት ጋር በነበረን የቲክቶክ መርሐ ግብር በሰፊው ዳስሰነዋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ በጥልቀት የዳሰስንባቸውን ነጥቦችና ዋና ዋና ትችታቸውን በቲክቶክ ላይ በነበረው ውይይታችን ያነሣነው ቢሆንም ያንን ላልተከታተሉትም ጭምር ይሆን ዘንድ አሰናድቸዋለሁና ተጋበዙ፡፡
በነገራችን ላይ ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጡ መልሶች ላይ እስከአሁን ባደረኩት ዳሰሰ፣ ‘እመቤታችን ቤዛዊተ ዐለም አይደለችም’ ከሚለው ትችታቸው ውጭ ጠቅላላ ስብከታቸውን ተመልክተው በዚያ ስብከት በኩል ከውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያን የተጮኹ የሌላ አካል ድምጾችን በተመለከተ ትችትና አስተያየት ሲሰጥ አላየሁም፡፡
ርብርቡንና የሁሉንም ጥረት ባደንቅም ሁሉም የተረባረበው አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑ ጉዳዩን ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል ባይ ነኝ፡፡ ለዚያ ነው ይኸንን ጽሑፍ ጨርሶ ማንበብ ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳትና የሊቀ ጳጳሱን መልእክት በጠቅላላው ለመረዳት ሊያግዝ ይችላል የምለው፡፡
ሙሉ ቪዲዮውን ተመልክቼ ስጨርስ አባ ገብርኤል ያቀረቧቸው ነቀፋዎች አንድ ቤተ ክርስቲያንን ‘ቤቴ፣ መጠጊያ፣ አካሌ’ ከሚል አባት ወይም መምህር ሳይሆን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ‘ጠላት፣ ሌላ፣ ውጭ’ አድርገው ከሚያዩት፣ ተሐዲሶና ፕሮቴስታንት በተደጋጋሚ የሚጮኹትን ጩኸትና እነሱን ተክተው፣ መስለውና አህለው የጮኹት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ነው ያደረሰኝ፡፡
መግቢያ
ስብከቱን የሰበኩት አባ ገብርኤል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ የሰበኩበት ቦታ ደግሞ ባለሃብቱ አቶ ጸጋየ ለስቅለት ባዘጋጀው የአዳራሽ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ እኔ የተመለከትኩት ስብከት የ51 ደቂቃ ቪዲዮ ነው፡፡
የስብከታቸው ርእስም ‘የሰባ ግብዣ’ የሚል ሲሆን ቅዱሳት መጻሕፍቱን በግእዝ ጠቅሰው፣ በአማርኛ ተርጉመው፣ በቀጥታ ወደ ራሳቸው ትችት የሚያዘነብሉበትን አካሄድ የተከተሉበት ነው፡፡ ርእሳቸውን የመረጡበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኢሳ 25፡ 6 ላይ ያለውን ወይገብር እግዚአብሔር በዝንቱ ደብር ለኲሉ ሕዝብ ከመ ይብልዑ መግዝአ ስቡሐ ወመሥዋዕተ ስሙረ፣ እነሆ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ በዚህ ታላቅ ተራራ የሰባ ግብዣን ያደርጋል፡፡ ያረጀ የከረመ፣ የቆየ የወይን ግብዣንም ያደርጋል፡፡ በወገኖች ላይ የተጣለውን መጋረጃ በአሕዛብ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛም ያስወግዳል የሚለው ነው፡፡
ጠቅላላ አስተያየት
ስብከቱ የተሰበከው ክርስቶስ በእለተ ዐርብ የከፈለውን የቤዛነት ሥራ ለማሳየትና የቀኒቱን ታላቅነት ለማጉላት ይመስላል፡፡ የመረጡትም ‘የሰባ ግብዣ’ የሚለው ርእስ አብ ለሰው ልጆች ያዘጋጀው፣ ያረጀ፣ የከረመ የወይን ጠጅ (ሊቀ ጳጳሱ ባይጠቅሱትም፣ ኢሳይያስ ያረጀ፣ ‘ያረጀ፣ የከረመ የወይን ጠጅ’ የሚለው የተጠቀመው ብሉየ መዋዕልነቱን ለማሳየት ነው) ሲሆን፣ ታላቅ ግብዣ የተባለበትም አንዴ ተበልቶ ለዘላለም የማያስርብ አስደናቂ ግብዠ በመሆኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ ስለ ሰባኪው አስተያየት ብንሰጥ፣ ርእስ አመራረጣቸውም ይሁን፣ ለመረጡት ርእስ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ጥንቅቅ ያሉ ናቸው፡፡ ግእዙንና አማርኛውንም በደንብ አድርገውና አቀናጅተው የሚጠቅሱ ብቻ ሳይሆኑ ንባባቱን የሚረዱበትና ለሰማዕያኑ የሚያቀርቡበት መንገድ ቀልብን የሚስብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከስብከታቸው ለመታዘብ እንደሞከርኩት ሁለት ወጥ ችግሮች አሉባቸው፡፡ 1ኛ) የመጻሕፍቱን ንባባት አስቀድመው በግእዝ፣ ከዚያ በአማርኛ ያስከትሉና ቀጥታ የሚገቡት የራሳቸውን ትርጓሜና ብይን ወደ መስጠት ነው፡፡ ይኸ ከተለመደውና በተጠቀሰው ንባብ ላይ ከጥንት ጀምሮ ሊቃውንቱ እንዴት እንደተረጎሙት፣ እንዴት እንዳመሰጠሩት ካስረዱ በኋላ ወደ ሕይወታችን መተርጎም የሚለው ስልት ያላገናዘብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ 2ኛ) በሚያነሧቸው ርእሰ ጉዳዮች ሁሉ ንባባቱን ለሐሜትና ሌሎችን ለመዝለፊያነት ወይም ትውፊትን ለማጣጣያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ይኸም በወንጌል ስም መሸቀጥ ወይም ወንጌል ለራስ ፍላጎት ማስገደድ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፣ ይኸ መንፈሳዊነት ሳይሆን ፖለቲከኝነት ነው የሚባለውም፡፡ አይደለም ወንጌል መድረክ ላይ ተቁሞ ሐሜት መቼም ቢሆን፣ የትም ቦታ ቢነገር ነውርም፣ ኃጢአትም ነው፡፡ ይኸ ወደ ጎን የሚተኩሱት ወይም ከውጭ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት ላይ የሚያደርጉት ተኩስ ጥሩ የነበረውን ትምህርታቸውን ፈጽሞ ገድሎባቸዋል፡፡
ዝርዝር ትችት
የእኔ ዝርዝር ትችት የሚያተኩረው ከጉዳዩና ከመረጡት ርእስ ጋር የማይገናኙ ወይም ባያካትትቷቸው ስብከታቸውን ሙሉዕ ከመሆን የማያግዷቸውን ነገሮች ብቻ ሳይሆን በዐላማና የተደራጀ በሚመስል በልኩ ባስተላለፏቸው ስሕተቶች ላይ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በቤተ ክርስቲያን ላይ ትችት አቅርበዋል ወይም የተሐዲሶና የፕሮቴስታንትን ድምጸት አስተጋብተዋል ብየ ስለለየሁ ስሕተቱ ከዚያ ቢልቅም ከዚህ ቀጥሎ የማተኩረው በአምስቱ ስሕተቶቻቸው ላይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለመከተል ይመቻችሁ ዘንድ የማደርገው ሊቀ ጳጳሱ የተናገሩትን በጥቅስ ውስጥ አስቀምምጥና፣ በማስቀጠል ትችቴን ወይም ጥያቄዎችን አስከትላለሁ፡፡
1) ከ13ኛው ደቂቃ ጀምሮ ስለ ኦሪት ያላቸው ትችትና ምልከታ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡
እንዲህ ይላሉ፣
‘የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፣ የኃጢአትም ኃይል ደግሞ ሕግ ናት ይላል፣ ኦሪት ይላታል፡፡ ኦሪት ገዳይ ነች፣ ጨካኝ ነች፣ ኦሪት ጥላ ናት፣ እግዚአብሔር ኦሪትን አሳልፏል፤ የኦሪቱ መሥዋዕት አልፏል፣ የኦሪት መሥዋዕት ወይም ሕገ ኦሪት ማለት የወላጅ ቤት ማለት ነው፡፡ እንደ እናት አባት ቤት የሚቆጠር፣ አንድ ሰው እናት አባቱ ቤት እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ነው የሚኖረው እንጂ እድሜ ልኩን ለእርሱ መኖሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን 40፣ 50 60 ዐመታቸው ድረስ ተዘፍዝፈው የሚኖሩ አሉ፣’
ይኸ ምልከታ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ ኦሪት ጨካኝ አይደለችም፣ ኦሪት ሞግዚት ነበረች፣ እናት ወንጌል እስከምትመጣ ልጆችን በአሳዳጊነት የጠበቀች ናት ኦሪት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‘ኦሪት ኃጢአቴን አበዛችብኝ’ ያለው፣ ሕግ የሚያስቀጡትን ነገሮች ዘርዝራ፣ ቆጥራ ስለምታሳውቅ ነው፣ ያለሕግ ሲያደርገው የነበረውን ሕግ ስትመጣ ስለከለከለችው ‘ቆጠረችብኝ፣ አበዛችብኝ’ አለ እንጂ ኦሪትን በሞግዚትነቷማ አመስግኗታል፡፡ ኦሪት የተሰጣትን ሚና ተወጥታለች፣ ኦሪት ያልተሰጣትን ታሳካ ዘንድ አልተጠየቅችም፣ በሌላ በኩል መጽሐፋዊው መረዳት ልጆች የወላጆች ወራሾች ናቸው፣ ‘በአባቴ ቤት መኖሪያ አዘጋጅላችኋለሁ’ ያለው ለዚያ ነው፡፡ የአባታችን ወራሾች ነን፡፡ የሊቀ ጳጳሱ ንጽጽርና ምሳሌም በዚህ ረገድ ደካማ ነው፡፡ በዋናነት ግን ይኸ ምልከታ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንታት ነው፡፡
ቀጥለውም ሌላ በጣም ጎደሎ ምሳሌ ይጠቀማሉ፣
‘ኦሪት ማለት ዋዜማ ማለት ናት፤ ዋዜማ ፍጹም በዓል ማለት አይደለችም፡፡ የእስራኤል ትልቁ ችግራቸው የኦሪቱን የዋዜማ ድግስ ከበቂ በላይ በልተው ሆዳቸው ስለሞላ ታላቁ የሐዲስ ኪዳን በዓል አምልጧቸዋል፡፡ ዛሬም ኦሪት ላይ ተቸክረው የቀሩ፣ በጽድቄ፣ በገድሌ በትሩፋቴ እድናለሁ ብለው እንደኩራት የሚናገሩ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ ደም የዘነጉና የረሱ ብዙዎች አሉ፡፡ ይኸንን ታላቁን የሰባ ግብዣ ከዚህ መመገብ ያቃታቸው፡፡’
እዚህ ላይ ዋዜማን በኦሪት፣ በዓልን ደግሞ በወንጌል መስለው ከተናገሩ በኋላ ከላይ እንዳልኩት ወደ ሐሜት ነው የገቡት፡፡ በመሠረቱ የአይሁድ ችግራቸው ሊቀ ጳጳሱ እንዳሉት ዋዜማውን ‘ከሚገባው በላይ በልተው በመጥገባቸው’ አይደለም፣ ዋዜማውማ የሚያጠግብ ቢሆን ምን ችግር ነበረው? ጉዳዩ ዋዜማው ያጠግብ ነበረ ወይ ነው? ያ ማለት ኦሪት ሰዎችን ማዳን ወይም መቤዥች ችላ ነበረ ወይ? የኦሪት ድግሱስ አንዴ ተበልቶ ለዘላለም የማያስርብ ነበረ ወይ? ኦሪት ካጠገበችማ የወንጌል መምጣት ለከንቱ ሆነ፡፡ ባይሆን አይሁድ ዋዜማውን አክብረው ዋናውን በዓል ሳያከብሩ ቀሩ ወይም በዋዜማው በቃቸው ቢሉ ያማረ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ከደቂቃዎች በፊት ‘ኦሪት ጨካኝ ናት’ ያለ ሰው ኦሪትን ዋዜማ፣ ወንጌልን ደግሞ በዓል ሲያደርቸው፣ ዋዜማን ጨካኝ እያላት እንደሆነ እንዴት ይዘነጋል? ዋዜማ ዋናውን በዓል መቀበያ ናት፣ መቆያ፣ ኦሪትም ዋናዋን እናት ወንጌልን ለመቀበል የቆየንባት ሞግዚት ሕግ ናት ቢሉ ያማረ ነበር፡፡
ሌላው በዚህ ክፍል ያቀረቡት ዘለፋ ነው፡፡ ‘ዛሬም ኦሪት ላይ ተቸክረው የቀሩ፣ በጽድቄ፣ በገድሌ በትሩፋቴ እድናለሁ ብለው እንደኩራት የሚናገሩ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ ደም የዘነጉና የረሱ ብዙዎች አሉ፡፡’
ይኸ ተሐዲሶና ፕሮቴስታንት ኦርቶዶክስን በተመለከተ የሚናገሩት እንቶፈንቶ የሆነ ሐሜት ነው፡፡ ይኸ ጽንፍ የያዘ ምልከታ እኛን አይመለከተንም፡፡ ሊቀ ጳጳሱን ከውጭ ወደ ውስጥ የጮኩት ያስባለን ይኸን መሰሉ ነው፡፡
አባታችን የአይሁድን ክፋትን ደግነት ባነጻጽሩበት ክፍል ላይም ሌላ ስሕተት ሠርተዋል፣ እንዲህ ይላሉ፣
‘እኔ መቼም የአይሁድ ከክፋታቸው ደግነታቸው በጣም ይከፋል፣ ከክፋት የከፋ ደግነት! ውኃ ጠማኝ ባለ ጊዜ ጉሮሮን የሚሰነጥቅ መራራ ሐሞት አቀረቡለት፡፡ እርሱን በመስቀል ላይ እየሰቀሉ፣ ይኸንን የመሰለ፣ ሥረ ወጥ የሆነ ልብስ መቀደድ የለበትም፡፡ ይልቁንም ለደረሰው ይድረሰው ብለው በልብሱ ላይ እጣ ተጣጣሉ፣ ያ ማለት ዐይንን አጥፍቶ ለግንባር እንደመጨነቅ፣ እግር ቆርጦ ለጫማ እንደማሰብ ማለት ነው፡፡ እነሱ ፍርፋሪ፣ ጨርቅ ላይ ነው የሚጣሉት፣ እኛ የጨርቅ ጉዳይ ሊያነጋግረን አይችልም፣ እኛ ጨርቅ ላይ አይደለንም፣ ዋናው ላይ ነው፣ መድኃኒቱ ላይ ነው፣ ፀሐይ ላይ ነው ያለነው፣ እኛ በጨረቃና በከዋክብት አንጨቃጨቅም፣ ዋናው ጸሐይ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ በቀራንዮ የተደገሰው ታላቁ ግብዣ፣ ሥጋየን ብሉ ደሜንም ጠጡ ብሉ ብሎ አሳልፎ የሰጠን በእውነት፡፡’
ይኸ ንግግራቸው በተጣርሶ የተሞላ ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት ከሊቃውንቱ ብሎም ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላቸው ነው፡፡ ሲጀምር አይሁድ ‘ተጠማሁ’ ሲላቸው ሆምጣጣ ማምጣታቸው ክፋታቸው እንጂ ደግነታቸው አይደለምና አባታችን በንጽጽሩ ለከንቱ ደከሙ፡፡ ሲቀጥል ልብሱን ሲካፈሉ አሁንም የክፋታቸውን ጥግ የሚያሳይ እንጂ እንዳልኩት ‘ዐይንን አጥፍቶ ለግንባር እንደመጨነቅ’ እንዳሉት ያለ ቅንጣት የመጨነቅ መንፈስ የለውም፡፡ ለአባታችን ችግር የሆነባቸው ንግግሩ የሳቸው ሳይሆን፣ የተሐዲሶ የፕሮቴስታንት እና ከውጭ ወደ ውስጥ የተጮኸ መሆኑ ነው፡፡
‘እኛ ጨርቅ ላይ አይደለንም’ ምን ማለት ነው? የክርስቶስ ጨርቁ ዋጋ የለውምና አይሁድ በመከፋፈል ደከሙ እያሉ ነው? አባታችን በርካቶች የቅዱሳንን ጥላቸውን፣ ጨርቃቸውን እየነኩ የሚፈወሱ መኖራቸውን አላነበቡም ይሆን? ወይስ ማጣጣል የፈለጉት ምንድነው? ‘ፀሐይ ላይ ነው ያለነው፣ እኛ በጨረቃና በከዋክብት አንጨቃጨቅም’ ማለትስ ምንድነው?
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታቱ ‘ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ፣ ዘአኰነኖ መዓልተ ለፀሐይ ከመ ያብርህ ለነ ውስተ ጠፈረ ሰማይ’ ካለ በኋላ ‘ፀሐይ ይበቃል’ ብሎ አልተወውም፡፡ ይልቁንም ‘ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ዘአኰነኖሙ ለወርኅ ወለከዋክብት ከመ ይሰልጡ ግብሮሙ በሌሊት’ በማለት ነው ያመሰገነው፣ ያደነቀው፡፡ አስተውሉ! ሊቁ በጥንቃቄ ነው ‘ግብሮም’ በማለት ጨረቃና ከዋክብትን ሥራቸው በሌሊት ይፈጽሙ ዘንድ አሠለጠናቸው ያለው፡፡ ‘ብርሃናቸውን ያበሩልን ዘንድ’ አላለም፣ የብርሃናቸው ምንጭ ፀሐይ መሆኑን ያውቃልና ሚና አላቀያየረም ወይም አልተምታታበትም፡፡ የጨረቃና የከዋክብት ግብራቸው ከፀሐይ የተቀበሉትን ብርሃን በሌሊት መግለጥ ነው፡፡ ፀሐይ የክርስቶስ፣ ጨረቃና ከዋክብት ደግሞ የቅዱሳኑ ምሳሌ የሆኑት በዚህ ንጽጽር ነበር፡፡ ጨረቃና ከዋክብት ከምንጩ ፀሐይ የተቀበሉትን ብርሃን በሌሊት ጨለማ እንደሚገልጡ፣ ቅዱሳንም ከፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ የተቀበሉትን ክብርና ጸጋ በሌሊት በሚመሰል ጨለማ ዐለምን ለማብራት ነው የሚተጉት (ከመ ይሰልጡ ግብሮሙ በሌሊት)፡፡ ‘ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ’ ያላቸው ደግሞ ራሱ ባለቤቱ ነው፡፡ ‘እኔ የዐለም ብርሃን ነኝ’ ካለ በኋላ ‘’እኔ ዐለምን ስላበራሁ እናንተ ምንም አታድርጉ’ አላለም፡፡ ይልቁንም ‘ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ። መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው አምላካችሁን ያመሰኙ ዘንድ’ እያለ አባታቸው ቅዱስ እንደሆነ እነሱንም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ አዘዛቸው እንጂ፡፡ ለዚያ ነው ይኸ የተቆነጸለ ትችትዎት ከመላዋ ወንጌል ጋር ያጋጫዎታል የምንለው፡፡ ለዚያ ነው ጩኸቱ ከንቱ የሆነ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንት እንቶፈንቶ ነው ያስባለን፡፡
2ኛ ከ20ኛ ደቂቃ ጀምረው ‘ነይ ነይ እምየ ማርያም ቤዛ ነሽ አሉ ለዓለም፣ እመቤታችን ቤዛ አይደለችም፣ ቤዛ ልጇ ነው፤ አትደንግጡ፣ ቤዛ ልጇ ነው፡፡ ነይ ነይ ቤዛ ነሽ አሉ ለዐለም ተብሎ አይሰበክም፣ ቤዛ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ነው፣’ የሚለው ንግግራቸው ነው፡፡ በዚህ ላይ ብዙዎች አስተያየት ስለሰጡበት በዚህ ጽሑፍ አልሄድበትም፡፡
3ኛ የክርስቶስን ፈራጅነትና አማላጅነት በተመለከተ ያለውን ፕርቶቴስታንታዊና ተሐዲሶዊ ትችት ከስብከታቸው ጋር የግድ የሚላቸው ባይሆንም ዐላማቸው ቤተ ክርስቲያንን መጎንተልን ከውጭ ሆኖ መተኮስ ነውን? በሚያስብል መልኩ ሮሜ 8፡34 አንሥተዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ፣
‘አሁን በእኛ ቤትና በሌላ ቦታ እንደትልቅ መጨቃጨቂያ ተደርጎ በሮሜ 8፡34 ምን የሚያከራክር ነገር አለው? መጽሐፍ ቅዱሱ የሚያከራክር ነገር የለምኮ፣ አባ ስረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ፣ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፣ በሉቃ 23፡ 34 ላይ ይኸ የተናገረው የይቅርታና የምልጃ ቃል ለዘላለሙ ሲያድን ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ይናገራል፣ አንድ ጊዜ የተናገረው ቃል ለዘላለሙ ይሠራል፡፡’
ይኸንንም ያነሡት ከውጭ ያሉት አካላት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያነሡትን ለማጥራት ቢሆን ኖሮ ባላስነቀፋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ‘አሁን በእኛ ቤትና በሌላ ቦታ እንደትልቅ መጨቃጨቂያ ተደርጎ’ የሚለው አባባል ራሳቸውን ሦስተኛ ወገን አድርገው ያቀረቡት፣ ኦርቶዶክስ ይኸንን የማታምንና የማታውቅ አስመስለው የሚከሱትን ክስ ያስተጋቡበት ሌላው ስሕተታቸው ነው፡፡ በመሠረቱ ለማብራሪያነት ያቀረቡት ጥሩ ቢሆንም በሌላው ቤት ‘አማላጅ ነው’ ሲሉ ምን እያሉ እንደሆነና ለምን እንደምንቃወም ሳይናገሩ ነገር ነው ጥቅሱን ለክስ ያነሡት፡፡
4ኛ ከ40ኛው ደቂቃ ጀምሮ ስለፍያታዊ ዘየማን ያንሡበትና በዚያው ላይ የትርጓሜ ባሕልና ትውፊትን አጥብቀው የተቃወሙበት ክፍል ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከ37ኛ ደቂቃ ጀምሮ በሰሙነ ሕማማቱ የምናደርጋቸውን መከራውን ማሰብን፣ ስግደቱን፣ ምንብባቱን የሚቃወም የሚመስል ንግግር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እኔን በጣም ያስገረመኝና በሕስተት የተሞላው ንግግራቸው ያለው በሚከተለው ውስጥ ነው፣
‘እንኳን ለእኛ ይቅርና በቀኙ የተሰቀለው ፍያታዊ ዘየማንን ታስታውሱታላችሁ? ሉቃ 23፡39 ላይ ያለው፣ ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ትመጽእ በመንግሥትከ በጣም ነው የምወደው ይኸን ሰው እኔ፡፡ እኛ በእንደዚህ ዐይነት መከራ ተይዘን ሳለን፣ በውኑ እግዚአብሔርን አትፈራውምን? እኔና አንተ የሚገባንን ቅጣት ተቀብለናል፣ ይኸ ግን ኃጢአት የለበትም፣ ማን ገለጸለት? ማነው ልቡን ያበራው? ማነው ዐይኑን ያበራው? ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ሰማዋ፣ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የሚለውን ቃል ነው፡፡ ሌላውን ድርሰት ተረት ተውት፡፡’
ሊቀ ጳጳሱ ይኸንን የሚሉት ስለፍያታዊ ዘየማን በትርጓሜው ውስጥ ያለውን ማንነቱን በተመለከተ የተቀመጠውን ታሪክና ሐተታ ነው ‘ድርሰትና ተረት’ የሚሉት፡፡ ይኸ የጥራዝ ነጠቆቹ የተሐዲሶን የፕሮቴስታንት ክስ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ንግግራቸውን ሲጨርሱ ስለምንተቸው አሁንም እንስማቸው፣
‘ስለዚህ ምን አለ? ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ትመጽእ በመንግሥትከ፣ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፡፡ አሳስብልኝ አላለም፡፡’
‘አሳስብልኝ አላለም፡’ ሲሉ አማላጅነትን እየተቃወሙ መሆኑን ልብ አድርጉ፡፡ ድምጹ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንት ነው ያልነው ይኸንንና መሰሉን ይዘን ነው፡፡ አሁንም እንስማቸውማ፣
‘በዚያ ያን የተዋረደውን፣ የተሰቀለውን፣ እርቃኑን እንደሱ የተሰቀለውን፣ የመንግሥት ባለቤት መሆኑን አውቆ መለኮታዊ እግዚአብሔር መሆኑን አውቆ፣ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፣ እስኪ እንደሱ እንሁን፣ እግዚአብሔር የዚህ ሰው እድል ይስጠን በእውነት፡፡ በጣም እድለኛ ሽፍታ ነው፡፡ እኛ መቀባባት ስለምንወድ፣ እንደዚህ፣ ተሸክሞ፣ ምርኩዙ ተሰብሮበት፣ እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው፤ ክርስቶስ እኮ ልዩነት ነው፣ ሁለቱ ሽፍቶች እንኳን ተለያዩ በክርስቶስ፣ ለመግደል የተባበሩ ነበር፣ ለመስረቅ አይለያዩም ነበር፤ ለመድፈር አንድ ነበርሩ፤ ችግር አልነበረባቸውም፣ ግን በክርስቶስ ተለያዩ፣ ለምን? ክርስቶስ እውነት ነዋ፡፡ እውነት አንዲት ቅንጣት፣ የማትከፈል፣ ጥያቄ የማይነሣባት፣ ኮሜንት የማይሰጥባት እውነት፣ ጌታው በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፡፡ በዚህ ደረጃ የተዋረደውን ሰው፣ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አውቆ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለ፡፡ ቤተልሔም ሲወለድና ሰብአ ሰገል ወርቅ እጣን ከርቤ ስያቀርቡለት አልነበረም፣ ፍያታዊ ዘየማን፣ ወደ ግብጽም ሲሰደድ አላየም፣ አልነበረም ፍያታዊ ዘየማን፣ ቃና ዘገሊላ ላይም አልነበረም በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ፣ ደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ አልነበረም፡፡ ሲጠመቅና አባቱ የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው ሲል አላየም አልነበረም፣ ነገር ግን ቀን አገናኛቸው፡፡’
አሁን ይኸንን በስሕተት የተሞላ ንግግራቸው እንተቸው፣ ‘እኛ መቀባባት ስለምንወድ፣ እንደዚህ፣ ተሸክሞ፣ ምርኩዙ ተሰብሮበት፣ እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር!’ የሚለው ንግግራቸው ችግር ያለበት ቁንጽልና ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንት ጩኸት ነው፡፡ ‘እኛ መቀባባት ሰለምንወድ እንጂ’ ያሉት የፍያታዊ ዘየማን ታሪክ በትርጓሜ መቀመጡንና መነገሩን ነው፡፡ ‘ፍያታዊ ዘየማን እመቤታችን ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ ላይ ካገኟት ሽፍቶች አንዱ ነበር’ የሚለውን ነው፡፡ አሁን ሊቀ ጳጳሱን ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል፣ ለመሆኑ እርስዎ ይኸንን ከመጻሕፍት ስላላገኙት አልቀበሉም እንበል፣ እርስዎስ ‘እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው’ ያሉት በምን ማስረጃ ነው? የዛን ቀን ብቻ ያየው መሆኑን ከየት አገኙት? ሁለቱ ሽፍቶችስ ሲሰርቁ ይተባበሩ እንደነበር አላዩ፣ አብረው አልነበሩ፣ ከየት አገኙት? የግል ትርጉምና ፍልስፍናዎትን ለማስተላለፍ የተጻፈንና ታሪክን ማጣጣል ምን የሚሉት ነው? ተቃርኖ አይታይዎትም ወይ? ሽፍታው ስለክርስቶስ አይቶም ይሁን ሰምቶ የማያውቅ መሆኑን ከየት ያልተጻፈ ነውና ከየት አመጡት? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ያስገድደናል፡፡
አምስት ገበያ ሕዝብ የሚያክል ይከተለው የነበረን ጌታ፣ የአይሁድና የሮማውያን አለቆች ‘ሕዝቡን ሁሉ ወሰደብን’ ብለው የቀኑበትን እርሱን፣ ሲወለድ የጥበብን ሰዎች በኮከብ ያስመራቸውና ቤተልሔም ያደረሰአቸውን እርሱን፣ በመወለዱ የተቆጣ ሄሮድስ ‘እገድለዋለሁ’ ብሎ 2000 ሕጻናትን የፈጀበትንና በይሁዳ ምድር ዐዲስ ክስተት የሆነውን እርሱን፣ ለምድራውያኑ ነገሥታቱ የሥልጣናቸው ተጋሪ መስሎ ጭንቅ የሆነባቸው እርሱን ከሕዝብ ወገን የሆነው ፍያታዊ ዘየማንን እንዲያው በጨበጣና በቆረጣ ‘እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው’ ሲሉ አልዘገነነዎትም ወይ? ፍያታዊ ዘየማን እኮ ጎልማሳ፣ ሽፍትነቱን ሐዋርያት ሳይቀሩ የመሰከሩበት፣ ታሪክ ያለው በምድር ላይ የኖረ ሰው ነበር እንጂ በእለተ ዐርብ ድንገት ከዐለት ሥር የበቀለ አይደለም፡፡ ያንን የሽፍታውን የቀደመ ታሪኩን ፈልጎ መዝግቦ ከሥሩ ለማስረዳት ሊቃውንቱ ያደረጉት ጥረት የሚያስደንቅ እንጂ እንዴት የሚያስተች መሰሎት? የዚህ ሁሉ ጣጣ ከውጭ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለጮኹ፣ ጩኸቱም የአባት ሳይሆን ለተሐዲሶና ፕሮቴስታንት በውክልና የተጮኸ በመሆኑ ነው፡፡
5ኛ በመጨረሻው ከ 47፡20 ጀምሮ ስለመስቀል ያላቸውን ተቃውሞ ያሳዩበትና በትርጉም ከመናፍቃኑ ጋር የተስማሙበት ጠባብ የሆነ ትርጉም ያለበትን ንግግር የተናገሩበት ነው፡፡ ይኸንን ብዙም አልሄድበትም፡፡ ልክ እንደቤዛ ትርጉም መስቀልንም መከራ ብቻ ተብሎ እንዲተረጎምና ዕፀ መስቀል ትርጉም የሌለው መስሎ አእንዲታይ ጥረት ያደረጉበት ክፍል ነው፡፡
በጠቅላላው ስብከታቸው በርካታ ችግሮች ያሉብት፣ ከውጭ ወደ ውስጥ የተጮኸ፣ ውጫዊ አካልን ለማስደሰት ወይም የሆነ አኩይ ዐላማን ለማስፈጸም የሚመስል ነቀፋ ወይም ትችት፣ ገፋ ሲልም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተደረገ፣ አሉባልታ ወይም የስሕተት ትምህርት ነው፡፡ ከላይ ትችት ያቀረብንባቸውን ንግግሮች ሳይጨምሩ የሰበኩት ስብከት ሰብከውት ቢሆን ኖር ስብከታቸው እንዴት ያማረ በሆነላቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ዋና በሚመስለው ስብከታቸው አስታከው ሊያስተላልፉት የፈለጉት ሌላ ‘ዋና መልእክት’ ከላይ የተቸነው በመሆኑ ምንም እንኳን ውድ ጊዜችንን

ቢሠዋብንም፣ ምንም እንኳን ትችቱም ሽቅብ ቢሆንብንም ይኸንን ማድረጋችን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ደኅንነት ሲባል የተጋባ ነበር፡፡ መሰል ክሶችን፣ ጩኸቶችንና ቁንጽላዎችን መታግስ ዋጋ አስከፍለውን ስለተማርን ወደፊትም ይኸንን በማድረጋችን እንቀጥላለን፡፡
ይኸው ነው!!!