ለ650 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲደርስ የነበረ የምግብ እርዳታ ሊቆም መሆኑ ተሰማ

ለ650 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲደርስ የነበረ የምግብ እርዳታ ሊቆም መሆኑ ተሰማ

(መሠረት ሚድያ)- የአለም ምግብ ፕሮግራም (World Food Programme) 10 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ርሀብ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ችግር አጋጥሟቸው እንደሚኝ ገልፆ ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለ650 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲያደርስ የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊያቆም መሆኑን ዛሬ አስታውቋል።

ከእነዚህ መሀል 3 ሚልዮን የሚሆኑት በጦርነት እና በከባቢ አየር ጠባይ መቀየር ምክንያት ተሰደው የሚገኙ መሆናቸውን የጠቆመው ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነ ተቋም 4.4 ሚልዮን የሚሆኑ እርጉዝ እና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ ለረሀብ ተጋልጠው ይገኛሉ ብሏል።

“በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ እና አፋር የህፃናት በምግብ እጥረት መዳከም ተከስቷል” ያለው የአለም ምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ባሉ ሀገራት ያሉ ግጭቶች ችግሩን እያባባሱ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።

ይህም አልበቃ ብሎ በመጪዎቺ ወራት በደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን የተተነበየ ሲሆን ይህም በሶማሌ ክልል ድርቅ እንዳያስከትል እንደተፈራ ጨምሮ ገልጿል።

በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት፣ የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም ዝርፊያ መሬት ላይ ያሉ ችግሮች ተብለው በዛሬው መግለጫ ላይ የተነሱ ሲሆን የአለም አቀፍ እርዳታ መቀነስ በዋናነት ተጠቅሷል።

“አዲስ እርዳታ ካልተገኘ በቀር ለ3.6 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን የምናቀርበውን እርዳታ በመጪዎቹ ሳምንታት ለማቋረጥ እንገደዳለን፣ አሁን ላይ ለ650 ሺህ ሰዎች ስናደርስ የነበረውን የነፍስ አድን እርዳታ እያቆምን ነው” ብሏል በመግለጫው።

ይህ አሳሳቢ ክስተት እንደ ቢቢሲ እና አልጀዚራ ባሉ አለም አቀፍ የሚድያ ተቋማት ሽፋን ቢያገኝም አንድም የመንግስት ሚድያ እስካሁን እንዳልዘገበው መሠረት ሚድያ ተመልክቷል፣ በመንግስት አካላትም የተሰጠ መግለጫ የለም።

ኢትዮጵያ ስንዴ ከራሷ ተርፎ ለውጭ ሀገራት መላክ እንደጀመረች ተደጋግሞ ቢገለፅም በርካታ ሚልዮን ዜጎች ርሀብ አጋጥሟቸው እንደሚገኙ የአለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎች ያሳያሉ።