የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ያስከተለው ምስቅልቅል እና ምሬት

[addtoany]

የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ያስከተለው ምስቅልቅል እና ምሬት

(መሠረት ሚድያ)- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ በተለይ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻ ከተደረገ ወዲህ የኑሮ ውድነት ተባብሶ ቀጥሏል።

የመገበያያ ዋጋቸው እጅግ እየጨመሩ ከመጡ ምርቶች አንዱ ነዳጅ ነው። የዛሬ ሁለት አመት በዚህ ወቅት ቤንዚን በሊትር 61 ብር ነበር፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 67 ይሸጥ ነበር፣ ኬሮሲንም በሊትር 67 ብር ነበር።

አሁን ላይ ቤንዚን 101 ብር ከ47 ሳንቲም ገብቷል፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 98 ብር ከ98 ሳንቲም ሆኗል፣ በሌሎች የነዳጅ ምርቶች ላይም በትንሹ ከ8 ብር በላይ ተጨምሯል።

ታድያ የዚህ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ የህዝብ ትራንስፖርቱ ዋጋም በእጅጉ እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል። በተለይ በተለይ በአዲስ አበባ ዳርቻ አካባቢዎች በሰፈሮችና በኮንዶሚኒየምዎች የሚኖሩ ዜጎች ለትራንስፖርት የሚያወጡት ወጪ እጅግ በጣም ጨምሮ ኑሮን እንዳከበደባቸው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

ለምሳሌ በኮዬ ፈጬ፣ በአራብሳ፣ በቂሊንጦ፣ በቱሉዲምቱ ወዘተ… የሚኖሩ ዜጎች ከነዚህ መኖሪያ መንደሮች እስከ መገናኛ እንኳን ለመድረስ በአውቶብስ 20 ብር፣ በታክሲ ደግሞ 50 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

“ወቅታዊ ታሪፉ ደርሶ መልስ በአውቶቡስ 40 ብር፣ በታክሲ 100 ብር ነው መገናኛ ድረስ ብቻ። እኛ ግን አልፈን ሄደን መሀል ከተማ ነው የምንሰራው፣ ለትራንስፖርት ብቻ በቀን እስከ 130 ብር በትሹ እናወጣለን” በሚል አስተያየት የሰጡት እነዚህ ዜጎች ይህንንም ለማግኘት ብዙ ተሰልፈው እና ተንገላተው እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ይሄ እጅግ በጣም ኑሮአችንን አክብዶብናል፣ ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል። አቤቱታችንን በሚዲያችሁ አስተላልፉልን፣ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል” የሚሉት እነዚህ ዜጎች የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ መነሳት ላልተጠበቀ እና እጅግ አቅምን ለሚፈታተን ከባድ ወጪ እንደዳረጋቸው በምሬት ይናገራሉ።

“በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ስራ ለመሄድ፣ ልጆችን ት/ቤት ለማድረስ እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን እንቅስቃሴ ሳይጨምር ለአንድ ሰው  ይሄን ያህል ወጪ በቀን እያወጡ እንዴት መኖር ይቻላል?” በማለት አስተያየታቸውን በጥያቄ ቋጭተዋል።