ወደ አራት መቶ የሚጠጉ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥሪ ማዕከል ሠራተኞች፣ “አይሶን ኤክስፔሪያንስ” በተሰኘ ወኪል ተቋም ይፈጸምብናል ባሉት የአሥተዳደር በደል ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
የሠራተኞች ማኅበር ሊቀ መንበሩ ሳላሃዲን ጀማል፣ ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማውን ካደረጉ ዛሬ ሁለተኛ ቀናቸውን እንዳስቆጠሩ ጠቅሰው፣ ሠራተኞቹ በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ የሆኑ አሥተዳደራዊ በደሎች እንደሚደርስባቸው ለዋዜማ ነግረዋታል።
ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ለማድረጋቸው፣ በወኪል ድርጅቱ በኩል የሚከፈላቸው ወቅቱን ያላገናዘበ ዝቅተኛ ክፍያ ዋነኛው ምክንያት መሆኑንም ነግረውናል።
ወኪል ድርጅቱ ከፍተኛ የሚባል ደምወዝ ይከፈላቸዋል የተባሉ ሠራተኞችን በተጠና መልኩ ከሥራ እንዲሰናበቱ ከማድረጉ ባሻገር፣ እጅግ ከባድ የሚባሉ መመዘኛዎችን በማውጣት ሠራተኞችን ከሥራ እያባረረ እንደሚገኝም ሰምተናል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ተመሳሳይ የሥራ አይነት የሚሰሩ ሠራተኞች፣ በቋንቋና ማንነት ልዩነት ብቻ የሚደረግ ሕገ-ወጥ የደሞዝ ልዩነትና አድሎ መኖሩን የማኅበሩ ሊቀመንበር ለዋዜማ ነግረዋታል።
በዚሁ የሠራተኞቹ አድማ ምክንያትም፣ ዛሬ ጥር 13፣2017 ዓ.ም እኩለ ቀን ድረስ፣ ሁሉም የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከላት ጥሪ እንደማይቀበሉ ዋዜማ ማረጋገጥ ችላለች።