ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥትን ተቸ !

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4/ቀበሌ 24/፣ በኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ በተፈጸመው የግፍ ግድያ እና በቀጠለው የጸጥታ ኀይሎች ማሸማቀቅ:

ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥትን ተቸ፤

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት በተጠመዱ የብዙኀን መገናኛዎች እና ፓርቲዎች ጉዳይ እየተወያየ ነው

• በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ አፈጻጸም ገመገመ፤
• “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት” በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው፣ በሕግ እንዲጠየቅ ቢወስንም፣ አፈጻጸሙን በዕርቅ ስም ያሰናከሉ አባቶችንና አካላትን በድክመት ገሠጸ፤
• “ሊፈጸም በማይችል የዕርቅ ሙከራ አዘናግታችኋል፤ የሰጣችኹትም ሹመት አግባብ አይደለም፤”

Image may contain: 1 person, sitting

ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ፤ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማን፣ ነገ ከቀትር በኋላ ያነጋግራል፤ መሥዋዕት በተከፈለበት እና አካል በጎደለበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራበት ይጠይቃል

• ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባውን እያካሔደ ነው፤

• የታሰሩት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ካህናት እና ምእመናን እንዲፈቱ፤ በጸጥታ ኀይሎች የሚደረግባቸው ማሸማቀቅም በአስቸኳይ እንዲቆም አሳሰበ፤

• በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4/ቀበሌ 24/ በሚገኘውና ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ሲጠየቅ በቆየው ቦታ፣ ስለተፈጸመው የግፍ ግድያ እና አሁንም ቀጥሎ ስለሚገኘው የጸጥታ ኀይሎች ማሸማቀቅ፣ ከአካባቢው የተወከሉ 15 ምእመናን ለምልአተ ጉባኤው ማብራሪያ ሰጥተዋል፤

• የቀድሞው ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከነበሩበት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት እንዲፈቀድላቸው ማመልከታቸውንና ይህም ጥያቄ፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጭምር ሲቀርብ መቆየቱን ምእመናኑ አውስተዋል፤

• ቦሌ መድኃኔዓለም፣ የካ ቅዱስ ሚካኤል እና የካሳንቺስ ቅዱስ ዑራኤል አብያተ ክርስቲያን ቢኖሩም፣ ለቀበሌው ርቀት ያላቸውና በተለይም ለአረጋውያን እናቶች እና አባቶች አድካሚ ስለኾነ፣ ይፈቀድልናል በሚል ቦታውን ሲጠብቁ መኖራቸውን አስረድተዋል፤

• ኾኖም፣ የፕላን ማሻሻያ በማድረግ ጭምር፣ “በመልካም ወጣት ማፍሪያ ፕሮጀክት” ስም ለሌላ ቤተ እምነት አራማጅ አሳልፈው ለመስጠት በአስተዳደሩ መወሰኑን ሲሰሙ፣ ቦታውን ለማስጠበቅ፣ መቃኞ ቤተ ክርስቲያኑን መሥራታቸውን ተናግረዋል፤ “በዚያው አካባቢ ከሠላሳ ያላነሱ አብያተ ጸሎት አሏቸው፤” በማለት የውሳኔውን ኢፍትሐዊነት እና አድሏዊነት ገልጸዋል፤

• የምእመናን ተወካዮቹን ማብራሪያ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ የተወያየው ምልአተ ጉባኤው፣ ከሕጋዊ አካል በሕጋዊ መንገድ ለቀረበ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ መስጠት እየተቻለ፣ ምእመናኑን ለአራት ዓመታት ከአጉላሉ በኋላ፣ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ሕይወት በግፍ በማጥፋት እና አካል በማጉደል የተወሰደው ሕገ ወጥ ርምጃ፣ “ከመንግሥት የማይጠበቅ ነው፤” በማለት ተችቷል፤ ባለአምስት ነጥቦች ውሳኔም አሳልፏል፤

• የመጀመሪያው፥ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማን ጠርቶ፣ መሥዋዕት የተከፈለበት ቦታ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ በሚፈቀድበትና የምእመናኑ የዓመታት ጥያቄ መፍትሔ በሚያገኝበት ኹኔታ ላይ ማነጋገር ነው፤ ኹለተኛው፥ ልጆቻችንን በግፍ የገደሉ፣ ያፈኑና ያሰሩ የጸጥታ ኀይሎች እና የአስተዳደሩ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቅ ነው፤ ሦስተኛው፥ ጥያቄ በማቅረባቸው የታሰሩት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ ገብረ ማርያምን ጨምሮ ካህናት እና ምእመናን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ነው፤ አራተኛው ደግሞ፣ ለተጎጂ ቤተ ሰዎች መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ነው፤ አምስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ፣ አሁንም በአካባቢው ተመድበው ነዋሪውን ምእመን እያሸማቀቁ ያሉ የጸጥታ ኀይሎች ከተግባራቸው በአስቸኳይ እንዲታቀቡ፤ የሚል ነው፡፡

• በውሳኔው መሠረት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማን ለማነጋገር፣ ለነገ ከቀትር በኋላ ቀጠሮ መያዙ ታውቋል፡፡

• በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው፣ በ“ኦሮሚያ ቤተ ክህነት”፣ የሐሰት ትርክት በማራገብ ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት ላይ በተጠመዱ የብሮድካስት ሚዲያዎች(ኦኤምኤን፣ ኤልቴቪ) እንዲሁም እንደ ኤፌኮ ባሉ ፓርቲዎች ሕገ ወጥ የጥላቻ እንቅስቃሴ ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተጠቁሟል፤ የሚመለከታቸውን ባለሥልጣናት ጠርቶ እንደሚያነጋግርም ይጠበቃል፡፡

Source – Hara Tewahido ሐራ ተዋሕዶ