ዘመነ ካሴ ነፃ ነህ መባሉ ተሰማ

ዘመነ ካሴ ነፃ ነህ መባሉ ተሰማ

(አዲስ ማለዳ) መስከረም ወር 2015 በቁጥጥር ሥር የዋለው ዘመነ ካሴ፤ ዛሬ ግንቦት 25 /2015 በባህርዳር ከተማ እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት “ነፃ ነህ” መባሉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

ዘመነ ካሴ በመስከረም ወር በቁጥጥር ሥር ውሎ መስከረም 23/ 2015 በባህርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ7 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቶት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ምርመራውን የያዘው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን “በተሰጠኝ 10 ቀናት ውስጥ ምርመራዬን ማጠናቀቅ አልቻልኩም” በማለት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

የዘመነ ካሴ ጠበቆችም ወንጀል የተባለውን ጉዳይ ለማጣራት በሚል ፖሊስ ላለፉት አራት ወራት ያጣራ በመሆኑ እና ፍርድ ቤቱ ባለፈው ችሎት ውሎ የፈቀደው 10 ቀናት በቂ መሆኑን እና ሌሎችን መከራከሪያዎች አቅርበዋል፡፡ ስለዚህም ”የጊዜ ቀጠሮ መስጠት አያስፈልግም“ በማለት ተከራክረው ዘመነ ካሴ በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤቱ ጠይቀዋል።

የምርመራ ቡድኑ ያቀረበው ምክንያት በቂ አይደለም ያለው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ የ7 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ፖሊስ እስከ ጥቅምት 01/2015 ድረስ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ ትዕዛዝ ተሰጥቶት፤ ዘመነ ካሴም ወደ ባህርዳር ማረሚያ ቤት መመለሱን ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

“በከባድ የሰው መግደል ወንጀል” ተከሶ የነበረው የዘመነ ካሴ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ መልስ ለመስጠት የክስ ችሎት ለማሰማት ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱም አይዘነጋም።

ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ በጠየቀው መሠረት ለኅዳር 12/2015 ቀን ዘጠኝ ሰዓት በድጋሜ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፤ ዘመነ ካሴ ለፍርድ ቤቱ የቃልና የጽሑፍ አቤቱታን እንዲያቀርብ ተደርጓል።

በመጨረሻም ዛሬ ግንቦት 25 /2015 ቀን ሰባት ሰዓት በዋለው ችሎት፤ ዘመነ ካሴ ከወንጀል ነፃ ነህ መባሉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ዘመነ ከማረሚያ ቤት እንዳልወጣ ማወቅ ተችሏል።