ይቅርታ ስናደርግ ካለፉት ስህተቶች ተምረን እንዳይደገሙ ከልብ በመስራት መሆን አለበት -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

“ይቅርታ ስናደርግ ካለፉት ስህተቶች ተምረን እንዳይደገሙ ከልብ በመስራት መሆን አለበት “ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የይቅርታ ቀን ሆኖ እየተከበረ ባለው የጳጉሜን አንድ እለትን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
እለቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ይቅር በመባባል ተጀምሯል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚህ ወቅት “በ2012 ዓ.ም በርካታ መልካምና የሚያኮሩ ተግባራትን እንዲሁም ሊደገሙ የማይገባቸው መጥፎ ጊዜያትን አሳልፈናል” ብለዋል።
መጪው አዲስ ዓመትም ለመልካም ሥራዎቻ እውቅና ሰጥቶ ማጠናከር የሚቻልበት እንዲሁም ከስህተቶች በመማር እርምት የሚወሰድበት መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት።
ለዚህ ደግሞ በዕለት ተዕለት የህይወት ክንዋኔዎች ውስጥ ይቅርታ ማድረግንም ሆነ መቀበልን መለማማድ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቷ መክረዋል።
“ነገር ግን ይቅርታ ስናደርግ ለታይታ ሳይሆን ካለፉት ስህተቶቻችን ተምረን እንዳይደገሙ ከልብ በመስራት መሆን አለበት” ሲሉም ገልጸዋል።
“አገር ያለ ሰው፤ ሰው ደግሞ ያለ መልካም እሴት ወደፊት መሄድ አይችልም” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ከዚህ አንጻር ዜጎች የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆኑ መልካም እሴቶችን አጥብቀው እንዲዙ ጥሪ አቅርበዋል።
በግለሰቦችና መንግስት መቀያየር መልካም እሴቶች ሊዋዥቁ እንደማይገባም ነው የገለጹት።
ከመልካም እሴቶች ዋነኛው የሆነው ‘ይቅርታ’ የአብሮነትና የጋራ ፍላጎት መገንቢያ መሳሪያ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።
ወጣቱን ትውልድ በመልካም እሴቶች መገንባት ከቻልን “አገር ትውደም ብሎ ሳይሆን ለአገር ጠበቃ ሆኖ በአደባባይ ይቆማል” ነው ያሉት።
ዛሬን ጨምሮ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያን መልካም እሴቶች የሚያጎለብቱ ስያሜዎች ተሰጥቷቸው በተለያዩ ተግባራት እንደሚከበሩ ታውቋል።