ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስከትሏል የተባለው አዲሱ የብሔራዊ ቴአትር ህንጻ ግንባታ
በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በማለም በ2011 ዓ.ም ላይ ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ፕሮፌሽናል ህንጻ ግንባታ በጊዜው ባለመጠናቀቁ በመንግስት ላይ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስከትሏል ተብሏል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከአፍሮ-ጽዮን ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ/ ጋር የህንፃውን ግንባታ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በሶስት ዓመት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ውል ተይዞ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይሁንእንጂ ተቋራጩ ኩባንያ በነበረው ደካማ አፈጻጸም በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 22% መስራት የነበረበት ቢሆንም መስራት የቻለው 6% ብቻ በመሆኑ በግንባታው ከፍተኛ መጓተት በመፈጠሩ፤ ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኦቪድ ግሩፕ ከተባለ አገር በቀል ድርጅት ጋር በቀጥታ ውል ተገብቶ የህንጻ ግንባታውን በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ በ2.9 ቢሊዮን ብር ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ፕሮፌሽናል ህንጻ ግንባታ በ6 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ 2B+G+11 ከፍታ እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡