ደብረጺዮን የአፍሪካ ሕብረት በአስቸኳይ በአፈፃፀም ሂደት ላይ እንዲያወያያቸው ጠየቁ

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ተከታታይ ከፍተኛ ቡድን በፍጥነት በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም ላይ እንዲወያይ መጠየቃቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ደብረጺዮን ይህን የጠየቁት፣ የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ተከታታይ፣ አረጋጋጭና ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ከፍተኛ ሃላፊ ኾነው አዲስ ከተሾሙት ሜጀር ጀኔራል ሳማድ አላዴ አሶዴ ጋር ዛሬ መቀሌ ውስጥ በተወያዩበት ወቅት ነው። ሕወሓት እና መንግሥት በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሠረት እስካሁን የፖለቲካ ውይይት እንዳልጀመሩና የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዳልተመለሰለት ደብረጺዮን መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። አፍሪካ ኅብረት ጀኔራል ሳማድን የሾመው፣ የሥራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁት ጀኔራል እስጢፋኖስ ራዲናን ምትክ ነው። ሕወሓት ከኮሚቴው ጋር በትብብር እንደሚሠራ ያረጋገጡት ደብረጺዮን፣ ኮሚቴው መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ በግልጽ በመለየት ሪፖርት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል ተብሏል።