“የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አመራር የነበረው የሾዴ መገደልን ተከትሎ ከቡድኑ ከድተው መንግስትን የተቀላቀሉ የቀድሞ ተዋጊዎች ቤተሰቦች ኢላማ ተደርገናል”- የቤተሰብ አባላት ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ሾዴ እየተባለ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (በመንግስት አጠራር ኦነግ ሸኔ) የቀድሞ ከፍተኛ አመራር በመከላከያ ሰራዊት መጋቢት 26, 2017 ዓ/ም መገደሉን ተከትሎ ቀደም ብለው ከቡድኑ ከድተው መንግስትን የተቀላቀሉ የቡድኑ ተዋጊዎች ቤተሰቦች እየተገደሉ እና እየተሰደዱ መሆናቸውን ለሚድያችን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የጃል መሮ ዋና ሰው የነበረው እንዲሁም በታንዛኒያው ድርድር ከጫካ ወጥቶ ታንዛኒያ ዳሬሰላም ድረስ ከመሮ ጋር ተጉዞ የሸኔ ሽብር ቡድን ተደራዳሪ የነበረው ሾዴ በተወሰደበት እርምጃ ተገድሏል” ማለቱ ይታወሳል።
ሾዴ ከታንዛኒያ መልስ የአጠቃላይ የወለጋ ዞኖች አዛዥ ተደርጎ በመሮ ተሹሞ የነበረ መሆኑንም መከላከያ አስታውቆ ነበር።
ይሁንና አመራሩ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሃሮ ሊሙ ወረዳ ገንጂ አካባቢ ከኮርማ ወንዝ ወደ ሱጊ በሚወሰደው መንገድ ላይ በሞተር ሳይክል ተደብቆ ሲጓዝ የፀጥታ ኃይሎች ባገኙት መረጃ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ እርምጃ እንደተወሰደበት መንግስት አስታውቆ ነበር።
ይህን ተከትሎ ግን በምስራቅ ወለጋ ዞን ሃሮ ሊሙ ወረዳ ጎርባ ጉዲና እና ሱጌ ቀበሌዎች የሚኖሩ እና ከወራት በፊት ከቡድኑ ከድተው መንግስትን የተቀላቀሉ የቀድሞ ተዋጊዎች ቤተሰቦች ኢላማ መደረጋቸውን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
“ከሾዴ ግድያ በሗላ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተጠያቂ ያደረገው የራሱን የቀድሞ ታጣቂዎች ነበር፣ እነዚህ ደግሞ ከድተው መንግስትን የተቀላቀሉት ናቸው” ያሉን አንድ የአካባቢው ነዋሪ የእነዚህ የከዱ ታጣቂዎች የትውልድ ቦታዎች ኢላማ እንደሆኑ ተናግረዋል።
“መጋቢት 30, 2017 ዓ/ም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት በሱጌ ቀበሌ የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች ቤተሰቦች ላይ ግድያ ፈፅመዋል፣ ሁለት ህፃናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች በዚህ እለት ብቻ ተገድለዋል” ያሉን አንድ የቤተሰብ አባል ሁለት ሌሎች ጎረቤቶችም ተጨምረው ተረሽነዋል ብለው ስማቸውን ለመሠረት ሚድያ አጋርተዋል (ስሞቻቸው: ዳባ ዘለቀ፣ ናቾ ደሳለኝ፣ አዳም ዘለቀ፣ ድሪባ ተስፋዬ፣ ሱካሬ ገመቹ፣ ቢቂልቱ ዲሪባ፣ ኢፍቱ ዲሪባ፣ ጋመዴ፣ ድሪባ፣ በቀለ ጎንደሬ እና ጆቴ በቀለ)።
ከዚህም በተጨማሪ መጋቢት 29, 2017 ዓ/ም ታጣቂዎቹ ወደ ሌላኛው ለመንግስት እጁን የሰጠ የቀድሞ ታጣቂ የትውልድ ቦታ ወደሆነው ጋርባ ጉዲና ቀበሌ በመግባት አምስት ሰዎችን እና የቤት እንስሳቶቻቸውን ይዘው እንደሄዱ ሌላ የቤተሰብ አባል ለሚድያችን ተናግረዋል።
“በአጠቃላይ የስምንት ቤተሰቦች አባላት በዚህ ድርጊት ከፍተኛ የሞት እና የእገታ ድርጊት ደርሶባቸዋል፣ ድርጊቱን ያመለጡት ወደ ሀሮ ከተማ ሸሽተዋል” በማለት የሆነውን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እድሜያቸው ከ7 እስከ 60ዎቹ የሚደርሱ የአቶ ሂርጶ ቤተሰብ አባላት ወደ ባሪሶ አካባቢ ተወስደው የነበረ ቢሆንም ሁሉም መገደላቸውን ትናንት መስማታቸውን የቤተሰቡ አባል አስረድቶ አሁን ሀዘን ተቀምጠው እንዳሉ ገልጿል።
በዚህ ዙርያ እካሁን በመንግስት አካላትም ሆነ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የተሰጠ መግለጫ የለም።