የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አውሮፕላን ነበራቸው?
ኢትዮጵያ ቼክ- የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮ/ል መንግስቱ ኀይለ ማርያም ይጠቀሙበት የነበረ ዳሽ ፋይፍ (ቡፋሎ) አውሮፕላን በአየር ኃይል የጥገና ሰራተኞች የጥገና ሥራ ተሰርቶለት ከ37 ዓመት በኋላ ለበረራ መብቃት መቻሉ በዛሬው እለት በመንግስት ሚድያዎች በስፋት ተዘግቦ ነበር።
እነዚህ ሚድያዎች በዘገባቸው ላይ “የቀድሞው ፕሬዝደንት መንግስቱ ኀይለ ማርያም አውሮፕላን” የሚል መረጃ ደጋግመው ሲጠቀሙ ታይተዋል፣ ይህም በበርካታ ህዝብ ዘንድ “ኮ/ል መንግስቱ ራሳቸው ብቻ የሚበሩበት (Presidential) አውሮፕላን ነበራቸው ማለት ነው?” የሚል ጥያቄን ጭሯል።
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የታሪክ ምሁርን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን መረጃ ጠይቋል።
“እርግጥ ነው፣ የመንግስት ሚድያዎቹ ሲፅፉት ‘የቀድሞው ፕሬዝደንት መንግስቱ ኀይለ ማርያም አውሮፕላን’ የሚል ሀረግ ተጠቅመዋል፣ ይህም አሳሳች ነው ምክንያቱም ኮ/ል መንግስቱ ለግላቸው ይጠቀሙበት የነበረ አውሮፕላን አልነበራቸውም። እንደ አሁኖቹ መሪዎች የውጭ በረራ ሲኖራቸው ይጠቀሙ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን ነበር” ብለው የታሪክ ምሁሩ ተናግረዋል።
አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀላፊ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ለመሠረት ሚድያ በላኩት ማብራርያ ይህንኑ ሀሳብ ተጋርተው “ይህ DHC 5 አውሮፕላን በመንግስቱ ግዜ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማ (livery) የተቀባ እና በአየር መንገዳችን ስር ይበር የነበረ ነው። ወዲያው ግን ከአገልግሎት ውጪ ተደርገው ነበር” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት የመንግስት ሚድያዎች በዚህ ዙርያ ባሰራጩት ዘገባ ላይ “የቀድሞው ፕሬዝደንት መንግስቱ ኀይለ ማርያም አውሮፕላን” በሚል ያቀረቡት መረጃ አሳሳች ሆኖ ተገኝቷል።
“ከዚህ አቀራረብ ይልቅ የቀድሞው ፕሬዝደንት ሲጠቀሙበት የነበረ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነበረ አውሮፕላን ተብሎ ቢቀመጥ ትክክለኛ ነበር” በማለት አስተያየታቸውን የቋጩት የታሪክ ምሁሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ ቼክ!