“ ራሳችንን ለአዲሱ የታሪፍ ስርዓት በሚገባ ለማዘጋጀት፣ የ90 ቀናት የእፎይታ ጊዜው እንደሚራዘም ተስፋ እናደርጋለን” – ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ
የአፍሪካ ሕብረት በአሜሪካ በተጣለው አዲስ ቀረጥ ላይ ስጋቱን ገለፀ።
የአፍሪካ ህብረት፣ የፕረዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ሀገራት ላይ የጣለው አዲስ ቀረጥ እንዳሳሰበው አስታወቀ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ፣ ፕረዝደንት ትራምፕ ያኖሩት አዲስ ታሪፍ/ቀረጥ፣ በአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ አሜሪካ በአፍሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው አዲስ ቀረጥ፣ የአባል ሀገራቱን ኢኮኖሚ ያዳክማል ” በማለትም አክለዋል፡፡
ፕረዝደንት ትራምፕ ያሳለፉት አዲስ የቀረጥ ውሳኔ፣ ከቻይና በስተቀር፣ በሌሎች ሀገራት ዘንድ ከሶስት ወራት በፊት እንዳይተገበር፣ ወይም ለ90 ቀናት ሳይተገበር እንዲቆይ አዘዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍም ፤ የአፍሪካ ሀገራት ውሳኔውን ለመተግበር በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ለ90 ቀናት እንዳይተገበር የተላለፈው ውሳኔ፣ ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡
“ ራሳችንን ለአዲሱ የታሪፍ ስርዓት በሚገባ ለማዘጋጀት፣ የ90 ቀናት የእፎይታ ጊዜው እንደሚራዘም ተስፋ እናደርጋለን ” ሲሉም ገልፀዋል ሊቀመንበሩ፡፡
የፕረዝደንት ትራምፕ አዲስ የቀረጥ ፖሊሲ፣ በተለይም እ.ኤ.አ ከ 2000 ዓ.ም ጀምሮ የአገዋ ዕድል ተጠቃሚዎች የሆኑ 32 የአፍሪካ ሀገራትን ይበልጥ ሊጎዳ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የአፍሪካ ሀገራት፣ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመቋቋም እንዲችሉ፣ የታሪፍ ከለላዎችን የማስወገደውን የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ስምምነትን (AfCFTA) ትግበራ እንዲያፋጥኑም ሊቀመንበሩ በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
የአህጉራዊው የነፃ ንግድ ስምምነት መተግበር፣ ከሌላው ክፍለአለም የሚመጡ መሰል ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ያስችላል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት፣ አህጉራዊውን የነፃ ንግድ ስምምነትና ሌሎችም አሰራሮችን በመጠቀም፣ እንዲህ ዓይነት ተግዳሮቶችን ወደ እድል እንዲቀይሩም ጠይቀዋል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ስምምነት፣ (AfCFTA) የአፍሪካ ህብረት እስከ 2063 ዓ.ም ድረስ ሊያሳካቸው ካነገባቸው አጀንዳዎች አንዱ ሲሆን፣ በተሳታፊ ሀገራት ብዛት፣ ከአለም ትልቁ የነፃ ንግድ ቀጣና እንደሆነ ይገለፃል፡፡
የነፃ ንግድ ቀጣናው፣ የአህጉሪቱን 1.4 ቢሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግና የአፍሪካ ሀገራትን በንግድ ግንኙነት የሚያስተሳስር እንደሆነም ይነገራል፡፡
የነፃ ንግድ ስምምነቱ፣ 90 ከመቶ በሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶች ላይ የሚጣሉ ቀረጦችን ሙሉ በሙሉ የማንሳት እቅድ ይዟል።