የአምናው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ዓላማ ተረሣ? ወይስ ዓላማው ሌላ ነበር?

የአምናው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ዓላማ ተረሣ? ወይስ ዓላማው ሌላ ነበር?
++++++++
(ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)
ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን እንደወሰነው ከሆነ ሰፊ የጳጳሳት ዝውውር ተፈጽሟል። ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደሌላው የተደረገው ይህ ዝውውር ትኩረትን የሚስበው ጳጳሳትን ማዘዋወር አዲስ ነገር ሆኖ ሳይሆን የተዘዋወሩት አባቶች እና ይዘዋቸው የነበሩት አህጉረ ስብከቶች ባለፉት ዓመታት ትልቅ መነጋገሪያ የነበሩ መሆናቸው ነው። በ2015 ዓ/ም በነበረው የቤተ ክርስቲያንችን ችግር ወቅት ዋነኛ አጀንዳ የነበረው ጉዳይ “እነዚህ አህጉረ ስብከት የሚመራቸው ተገቢ የሆነ አባት የላቸውም” የሚል ነበር።

በወቅቱ የተዘገበው እንዲህ ይነበባል። “የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው አጀንዳዎች መካከል የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና ሢመት አንዱና ዋነኛው ነው። በመሆነም በጉዳዩ ዙሪያ ለሦስት ቀናት ከተወያየ በኋላ ለአሁኑ ችግር ባላባቸውና አስፈላጊ በሆነባቸው ዘጠኝ አህጉረ ስብከት ላይ በዚህ ዓመት 2015 ዓ/ም ዘጠኝ አዳዲስ ኤጲስ ቆጳሳት እንዲሾሙና በጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን እውነትና ቀኖናን እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲሁ አባቶች በሚያስፈልጉባቸው አህጉረ ስብከት የአዳዲስ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት” ሲመት እንዲፈጸም ተወስኗል።

በዚህም መነሻ ለአካባቢዎቹ ተስማሚ ናቸው፣ አካባቢዎቹን ያውቃሉ፣ ቋንቋዎቹን ይናገራሉ የተባሉ አባቶች በመብራት እንዲፈለጉና እንዲሰየሙ ሰፊ ሥራ ተሠራ። በሚካሄደው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙ አባቶች የሚመደቡባቸው የዘጠኙ አህጉረ
ስብከት ስም ዝርዝርም ተለይቶ ተነገረ። እነዚህም “፩. ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት፣ ፪. ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፣ ፫. ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት፣ ፬. የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት፤ ፭ ምዕረብ አርሲ ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት፣ ፮. ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፣ ፯. ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት፣ ፰. ጌዴኦ ቡርጅና አማሮ ሀገረ ስብከት፣ ፱. ዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት” ናቸው በሚል ተዘግቦ ነበር።

ቀጥሎም ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በተገኙ 34 አባላት በተደረገ ምስጢራዊ ነው በተባለ የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት 1. አባ ሣህለ ማርያም ቶላ – ከ34ቱ/31 ድምፅ በማግኘት ለምዕራብ አርሲ – ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት፣ 2. አባ ወልደ ገብርኤል አበበ – ከ34ቱ/18 ድምፅ በማግኘት ለምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፤ 3. አባ ጥላሁን ወርቁ – ከ34ቱ/26 ድምፅ በማግኘት ለምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፤ 4. አባ ዓምደ ሚካኤል ኀይሌ ከ34ቱ/30 ድምፅ በማግኘት ለሆሮ ጉድሩ ወለጋ – ሻምቡ ሀገረ ስብከት፤ 5. አባ ኀይለ ማርያም ጌታቸው – ከ34ቱ/28 ድምፅ በማግኘት ለድሬዳዋ ሀገረ ስብከት፤ 6. አባ ዘተክለ ሃይማኖት ገብሬ – ከ34ቱ/20 ድምፅ በማግኘት ለምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት፤ 7. አባ እስጢፋኖስ ገብሬ – ከ34ቱ/18 ድምፅ በማግኘት ለቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት፤ 8. አባ ክፍለ ገብርኤል ተክለ ማርያም – ከ34ቱ/32 ድምፅ በማግኘት ለጌድኦ አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት፤ 9. አባ ስብሐት ለአብ ኃይለ ማርያም – ከ34ቱ/31 ድምፅ በማግኘት ለዳውሮ እና ኮንታ ሀገረ ስብከት ኾነው፣ በምልአተ ጉባኤው አብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል ተብሎ ታወጀ፡፡

ቀጥሎም በቅድስት ቤተክርስቲያን የተሰጣቸውን ሥያሜ ይዘው ለተጠቀሱት አህጉረ ስብከት ተመደቡ።
፩- ቆሞስ አባ ክንፈገብርኤል ተክለማርያም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ተብለው ተሠይመው ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፤
፪- ቆሞስ አባ ሣህለማርያም ቶላ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተብለው ተሠይመው ለምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፤
፫- ቆሞስ አባ ስብሐትለአብ ኃይለማርያም ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተብለው ተሠይመው ዳውሮና ኮንታ ሀገረ ስብከት፤
፬- ቆሞስ አባ አምደሚካኤል ኃይሌ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተብለው ተሠይመው ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፤
፭- ቆሞስ አባ ኃይለማርያም ጌታቸው ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ተብለው ተሠይመው በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት፤
፮- ቆሞስ አባ ጥላሁን ወርቁ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ተብለው ተሠይመው በቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት፤
፯- ቆሞስ አባ ዘተክለሃይማኖት ገብሬ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ተብለው ተሠይመው በሆሮ ጉድሩ ሀገረ ስብከት፤
፰- ቆሞስ አባ እስጢፋኖስ ገብሬ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ተብለው ተሠይመው በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት፤
፱- ቆሞስ አባ ወልደገብርኤል አበበ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ተብለው ተሠይመው በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፤

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በወቅቱ እንደተናገሩት “ቀኖና በመሻር” ጭምር ነው ለነዚህ አካባቢዎች አባቶች የተሾሙት። ያ የቀኖና ሽረት እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ማመቻመች ዛሬም ድረስ ያልተወጣነው ውጥንቅጥ ውስጥ እንደከተተን ይታወቃል። በሚገርም ሁኔታ ግን አዳዲሶቹ ጳጳሳት በተመረጡ በዓመቱ ለመመረጣቸው ምክያንት የሆኑት አህጉረ ስብከቶች በሌሎች አባቶች እንዲተኩ፣ አዳዲሶቹ ደግሞ ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲዛወሩ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት፦
1ኛ. ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ ምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት፤
2ኛ. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ከምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ ኢትዮ ሱማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት፥
3ኛ. ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ከምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ አፋር ሀገረ ስብከት፤
4ኛ. ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ከኢትዮ ሶማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ወደ ምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ተዛውረው አህጉረ ስብከቱን በአባትነት እንዲመሩ፤
5ኛ. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኤድመንተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲመደቡ፤
6ኛ. ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አሁን በያዙት የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ላይ ከንባታ፣ሀላባና ጠንባሮ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፤
7ኛ. ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል አሁን የያዙትን አህጉረ ስብከት እንደያዙ የምሥራቅ ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የሆሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ ተወሰነ።

ይህ ዝውውር የተከናወነው አምና በተሾሙት በአዳዲሶቹ ጳጳሳት በመስማማታቸው ጭምር እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ጥያቄው “ከነዚህ አህጉረ ስብከት የሚነሡ ከሆነ ከመጀመሪያውኑ ለምን ነበር የተሾሙት?” የሚል ነው።

በአምናው የአዳዲስ ጳጳሳት ሲመት ላይ ትልቅ ተዋናይ የነበሩት እና ደራርበው ይዘዋቸው ከነበሩት አህጉረ ስብከት ላይ ቀንሰው ለአዳዲሶቹ እንዲያካፍሉ የተደረጉት አቡነ ሩፋኤል ልክ በዓመቱ እነዚያን አህጉረ ስብከት ደግመው እንዲጠቀልሉ የተደረገበት ምሥጢር ምን ይሆን? “ንፁህ ኦሮሞ ሹመንልሃል” ባሉ በዓመቱ እነዚያን “ንፁህ ኦሮሞዎች” ወደ ሌሎች ሀገረ ስብከቶች ያዘዋወሩት “ለኦሮሞዎቹ ጥቅም” ይሆን? ወይንስ “ኦሮሞ አሁን ፓትርያርክነት ተራው ነው” ካሉት ነገር ጋራ የተገናኘ ነገር አለው? ቅዱስ ሲኖዶስ በየዓመቱ በዚህ መልኩ ከውጪ ለሚመለከተው ሰው ሳይቀር በሚያሳዝን ሁኔታ ተግባሩን የሚፈጽመው እስከ መቼ ነው?