አሜሪካ ምን አለች ?
➡️ ” ፋኖ ተጨባጭ እና ሰላማዊ የሆነ ዓላማ ይዞ ይምጣ። ”
➡️ ” የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ለማስቆም ድርድሩን ይቀጥል። ”
➡️ ” የፌዴራል መንግሥት በራሱ ዜጎች ላይ የሚያደርገውን የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ ያቁም። ”

አሜሪካ ዛሬ አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲዋ በኩል ለፌዴራል መንግሥት እና ለታጣቂዎች መልዕክት አስተላልፋለች።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት በመላው ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት የዳረጉ ግጭቶች ሰላማዊና ትክክለኛ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደሩ፥ ለታጣቂ ኃይሎች እና ለፌደራል መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት ህዝብን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል።
” ጦርነቱን ማቆም፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መርዳት እና ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
” በትጥቅ ትግል ስም የሚፈጸሙ ህገወጥ እና የኃይል እርምጃዎች ሊቆሙ ይገባል ” ብለዋል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በመልዕክታቸው ለፋኖ ፣ ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) እና ለፌደራል መንግስት የተናጠል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህም ፥
– ፋኖ ተጨባጭ የሆነ እና ሰላማዊ የሆነ ዓላማ/ግብ ይዞ እንዲመጣ፤
– የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ደግሞ በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ለማስቆም ድርድሩን እንዲቀጥል፡
– የፌደራል መንግስት በራሱ ዜጎች ላይ የሚያደርገውን የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆምና ረጅም እርምጃ ወደ ለሰላም በመምጣት መፍትሄዎችን እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደሩ በመልዕክታቸው ማጠናቀቂያ ” ሰላምና መረጋጋት የምንመርጥበት ጊዜ አሁን ነው ” ብለዋል።