“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ”
===================
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
በሀገር ውስጥና በልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-
በመዋዕለ ጾሙ ሰይጣንንና መስሓቲ ተግባሩን ድል በማድረግ ድል እንድንነሣ ያደረገን ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ኣርብዓ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!
‹‹ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር በዘትክሉ ተቃውሞቶ ለመናግንተ ሰይጣን፤ የሰይጣንን ሽንገላ መቃወም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ›› (ኤፌ.፮፥፲፩)
እኛ ሰዎች ቀዋሚና ምሕረት የለሽ ጠላት እንዳለን እናውቃለን። ይህ ጠላት ሰይጣን፣ ዲያብሎስ፣ክፉ መንፈስ፣ ርኩስ መንፈስ ተብሎ እንደሚጠራም ቅዱስ መጽሐፍ ነግሮናል። ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ በክፉ ሽንገላው ሰዎችን ሲጥል ኖሮኣል። አሁንም ከዚህ ክፉ ተግባሩ አልታቀበም። ለወደፊቱም ይታቀባል ተብሎ አይጠበቅም። ጌታችን በዚህ ዓለም በሥጋ በተገለጠ ጊዜም ይህ ክፉና ርኩስ መንፈስ በሽንገላ ቃሉ ጌታችንን ሊጥል ያልተሳካ ሙከራ አድርጎአል፡፡ ርኩሱ መንፈስ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን እንደሚያቀዳጅ ያውቃልና፣ ጌታችን ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ኣርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾሙን ተመልክቶ፣ በሽንገላ ቃሉ ሊጥለው ሙከራ አድርጎአል።
ይህንን ያደረገበት ዋና ምክንያትም ጾም መንፈሳዊ ኃይል መሆኑን በውል ያውቃልና በጾም ኃይል ከእጄ ያመልጣል ብሎ በማሰቡ ነው። ይሁን እንጂ ሰይጣን የሰውን ደካማ ጠባይ በመጠቀም ያስለመደው ሽንገላ በተዋሕዶ ሰውም አምላክም በሆነው ጌታችን ላይ ሊሳካለት ባለመቻሉ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ሊሄድ ችሎአል፡፡
የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!
የጌታችን ድል አድራጊነት ያስተማረን ብዙ ነገር አለ። በዚህ ተግባራዊ ትምህርቱ እኛ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል የምናደርግባቸው ሁለት መሣሪያዎችን በዋናነት አሳይቶናል። እነሱም የእግዚአብሔርን ጋሻ መልበስና በጾም መንፈሳዊ ኃይልን መቀዳጀት ናቸው፡፡
ሁሌም እንደምንማረው በውስጣችን ሁለት ተቃራኒ ነገሮች አሉ። እነሱም ፍትወተ ሥጋና ፍትወተ መንፈስ ናቸው። እነኝህ ሁለት ነገሮች አንዱ ላንዱ ፍጹም ተቃራኒ መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያስረዳል። “እስመ ሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ፤ ወመንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ፤ ወይትአበዩ በበይናቲሆሙ ከመ ኢትግበሩ ዘትፈቅዱ፤ ወባሕቱ እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግበሩ” ማለትም “ሥጋ መንፈስ የማይወደውን ይወዳል። መንፈስም ሥጋ የማይወደውን ይወዳል። እርስ በርሳቸውም ይቀዋወማሉ። ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋን ምኞት ግን ከቶ አትፈጽሙ” (ገላ.፭÷፲፮‐፲፰)፡፡
እነኝህ የውስጣችን ጠባዮች በዚህ ደረጃ እርስ በርስ የሚቃረኑ መሆናቸው ለምናስተውላቸው በግልጽ የሚታወቁ ናቸው። ከዚህ አንጻር ሰይጣን ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ የሥጋችንን ፍላጎት እንድንከተል ይገፋፋናል። መሣሪያዎቹ ደግሞ ፍቅረ መባልዕት፣ ፍቅረ ንዋይና ፍቅረ ሢመት ናቸው። ይህም በመሆኑ ነው ሰይጣን በነዚህ ጌታችንን ሊሸነግለው የሞከረው። ይሁንና ጌታችን እነኝህን የሽንገላ መሣሪያዎች ሰባብሮ ጥሎአቸዋል። የጣላቸውም በጾምና በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ጾም መጾም ማለት ከፍቅረ መባልዕት፣ ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሢመት ፍላጎት ጨርሶ መራቅ ማለት ነው። ይህንን አደረግን ማለት ደግሞ ሥጋችን የማይወደውን፣ መንፈሳችን ግን የሚወደውን ነገር አደረግን ማለት ነው። ይህ ሲሆን ሰይጣን ከሰረ፤ ድልም ሆነ ማለት ነው። በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ዲያብሎስ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ይሄዳል፡፡
ከዚህ አኳያ እኛም በቃለ እግዚአብሔር እየተመራን የምንጾምበት ምክንያት የሥጋችንን ፍላጎት በመግራት ለነፍሳችን ፍላጎት ለማደርና በዚህ ኃይለ መንፈስ ሰይጣንን በማሸነፍ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለመሆን ነው፡፡
የተከበራችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!
የጾም ዋና ዓላማ ሥጋዊ ፍላጎትን መግራት፣ በምትኩ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትን ማጐልበት እንደሆነ ተነግሮናል። በመሆኑም ይህንን መርሕ ጠብቀን መጾም ግዴታችን ይሆናል። ዛሬ ባለንበት ዓለም ሥጋዊ ፍላጎታችን ያየለበት፣ መንፈሳዊ ፍላጎታችን ግን የተዳከመበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከመራራት ይልቅ ጭካኔ፣ ከእምነት ይልቅ ክሕደትና አስመሳይነት በዓለማችን ላይ የበላይነቱን ይዞ መገኘቱ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ይሁንና ዓለም ቢሰማም ባይሰማም፣ ሐቁም ጠቃሚውም የመንፈስን ፍላጎት ማጎልበት ስለሆነ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ማለትም ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ርኅራኄንና ሃይማኖትን ማስፈን ምርጫችን ልናደርግ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንም እንድንጾም የምታስተምረን እነዚህን ለመተግበር ጾም ፍቱን መሳሪያ ሆኖ ስለሚገኝ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የጾም ዓላማውና ግቡ ጽኑዕ ሃይማኖትን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ልባዊ አንድነትን፣ የማይናወጽ ፍትሕንና እኩልነትን፣ ወሰን የሌለው ርኅራኄን በውስጣችን ብሎም በዓለማችን ማሥረጽ እንደሆነ በውል ተገንዝበን ጾሙን መጾም ይገባል። ልንለብሳቸው የሚገቡ እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የእግዚአብሔር ጋሻዎች ናቸውና፡፡ ይህንን ካደረግን እንደ ጌታችን የሰይጣንን ሽንገላ በጣጥሰን በመጣል በአስተማማኝ ሁኔታ ድል ማድረግ እንችላለን፤ የተጠራነውም ለዚሁ ነው፡፡
በመጨረሻም፡-
የሕዝባችንና የሀገራችን የራስ ምታት ሆኖ የሚገኘውን ያለመግባባት ዝንባሌ ለመቅረፍ ከልብ በመጸለይ፣ እንደዚሁም የተራቡትን በማጒረስ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ፍትሕ ለተነፈጉትም እውነተኛ ፍትሕን በመስጠት፣ መዋዕለ ጾሙን እንድንጾመው በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፡፡
የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ