ከመገናኛ አንስቶ እስከ ደብረብርሃን ነባር የአማራ ይዞታዎችን የማፍረስና አማራዎች እየተለዩ ልዩ የማቆያ ስፍራ ተወስደው የሚመረመሩበት እቅድ ተነድፎ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑ ታወቀ።
ከመገናኛ አንስቶ፣ ኮተቤ፣ ካራ፣ ለገጣፎ፣ ሰንዳፋ፣ አሌልቱ፣ ሸኖ ፣ ጫጫ አድርጎ ደብረብርሃን ድረስ የሚዘልቀው ይህ አማራውን ነባር ይዞታ የማሳጣትና ባለፉት አመታት የገነባውን ማሕበራዊ ትስስር የመበጠስ እንቅስቃሴ ለበርካታ ወራት አገዛዙ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግበረ ኃይል ብሎ የሚጠራቸው መከላከያ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት (ኢንሳ) ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተውጣጣ ኮሚቴ ሲሰራበት ቆይቶ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ ነው የተሰማው።
በሬድዋን ሁሴንና በትዕግስት ሀሚድ በበላይነት የሚመራው ይህ አማራውን አንገት ለማስደፋት የሚደረግ እንቅስቃሴ፣ ከነባር ይዞታው ከማባረር ከማፈናቀል ባሻገር እስከ ሀብት ንብረቱን ማሳጣት፣ በሕጋዊ መንገድም ቢሆን የታጠቀውን መሳሪያ ማስፈታት ድምፅ አልባ መሳሪያን ጨምሮ መንጠቅ የሚሉት እንደሚገኙበት ኢትዮ 251 ሚዲያ ሰምታለች።
እነዚህ የተለዩት አካባቢዎች ፋኖ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ቢጀምር መንገድ ጠራጊና ደጀን ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ተብሎ በጥናቱ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል።
ባለፉት ጊዜያት ሸዋ ላይ ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነት አቋርጦ ኤሊት ፎርስ የሚለውን በሔሊኮፍተር አስገብቶ ዘመቻ ያደረገው የዚሁ እቅድ አንዱ አካል እንደሆነ ምንጮች አክለው ለኢትዮ 251 ሚዲያ ገልፀዋል።
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘውንና ሸዋ ላይ የሚንቀሳቀሰውን ፋኖ ቢቻል ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ካልተቻለ ግን ማዳከምና ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የእቅዱ አንዱ አካል እንደሆነ ታውቋል።
ኢትዮ 251 ሚዲያ