” ሰላም ፈላጊ ነን ማለት ግን ራሳችንን የመከላከል ፍላጎት የለንም ማለት አይደለም ” – የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት

” ሰላም ፈላጊ ነን ማለት ግን ራሳችንን የመከላከል ፍላጎት የለንም ማለት አይደለም ”  – የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት

በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት የተመሠረተበትን 51ኛ ዓመት (የካቲት 11) በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት በመቐለ ከተማ በሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ሥር የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥና የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኖ ነበር።

በዚሁ መርሐ-ግብር ላይ የተገኙት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌ/ጀ ታደሰ ወረደ እና የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌ/ጀ ታደሰ ወረደ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውን የጦርነት ጠባሳ በማስታወስ ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን ቀሪ ጥያቄዎች በሰላም እንዲፈቱ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል።

ተፈናቃዮችን መመለስ እና የትግራይን ግዛታዊ አንድነት ማረጋገጥ ” ህጋዊ፣ ፍትሃዊ እና ብሔራዊ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች ናቸው ” ብለዋል።

እነዚህን ጥያቄዎች በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት አስተዳደራቸው የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

” ባለፈው ጦርነት ከባድ ውድመት ደርሶብናል ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተጨማሪ መስዋዕትነትና የአካል ጉዳት ሳይከተል ለቀሪ ጥያቄዎች መፍትሔ እንዲመጣ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ሰላም ፈላጊነታቸው ድክመት እንዳልሆነ ሲያስረዱም ፥” ሰላም ፈላጊ ነን ማለት ግን ራሳችንን የመከላከል ፍላጎት የለንም ማለት አይደለም ” ብለዋል።

” የሚቻለንን ሁሉ ሰርተን ጦርነት በማስቀረት የተረበሸውን ህዝባችንን እንዲረጋጋ እንሰራለን ” ሲሉም ተደምጠዋል።

በሌላ በኩል የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥብቅ የትችትና የክስ መልዕክት ሰንዝረዋል።

” የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ሦስት ዓመታት ቢያልፉም፣ ስምምነቱ በተሟላ መልኩ ባለመተግበሩ ሕዝቡ አሁንም በመከራ ውስጥ ይገኛል ” ሲሉ ገልጸዋል።

” የፌዴራል መንግሥት የሰላም ስምምነቱን በመጣስ በትግራይ ላይ ተኩስ ከፍቷል ” የሚል ክስም ሰንዝረዋል።

” በትግራይ ላይ ያንዣበበው አደጋ በውይይት የማይፈታ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ ህልውናውን ለማስቀጠል ወረራን የመመከትና ራሱን የመከላከል ግዴታ ውስጥ ይገባል ” ሲሉ ተደምጠዋል።

የሁለቱ መሪዎች ንግግር በትግራይ ክልል እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ዳግም ወደ ውጥረት እያመራ መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል ተብሏል።