እናት ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደመሠረቱት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተባለውን ቅንጅት እንዲቀላቀል እንደፈቀደለት አስታወቀ። ፓርቲው፣ እናት ፓርቲ መስራች የሆነበት ቅንጅት ሕጋዊ አባል እንዲሆን ቦርዱ ከወራት ውዝግብ በኋላ በመፍቀዱ ምስጋናውን ገልጧል። እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ ባለፈው መስከረም “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተባለውን ቅንጅት መስርተው ምርጫ ቦርድ እንዲያጸድቅላቸው ሲጠይቁ፣ ቦርዱ የእናት ፓርቲን አባልነት ውድቅ በማድረግ አራቱ ፓርቲዎች ብቻ የቅንጅቱ አባል ናቸው በማለት መወሠኑ ይታወሳል። ቦርዱ የእናት ፓርቲን አባልነት ያላጸደቀው፣ ፓርቲው አስፈላጊ ሰነዶችን እንዳላሟላ፣ ፓርቲው ቅንጅቱን መቀላቀሉን የሚቃወሙ የፓርቲው አባላት መኖራቸውን እና የቅንጅቱን ምስረታ ያጸደቀው የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባኤው የተሟላ እንዳልነበር በመግለጽ ነበር። በዚሁ ሳቢያ ፓርቲውና ቦርዱ ሲካሰሱ ቆይተው ነበር።