በሽፋን ምርመራ ወቅት “ከግድያ በስተቀር” የሚፈጸም ወንጀልን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው አወዛጋቢ ድንጋጌ ተሰረዘ
በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን “በሽፋን ስር” ሆኖ የመመርመር ኃላፊነት የተሰጠው ሰው፤ “ከግድያ በስተቀር” የሚፈጽማቸውን የወንጀል ድርጊቶች ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው ድንጋጌ ተሰረዘ። ድንጋጌው የተሰረዘው አዋጁ “በሰፊው እንዲተረጎም ስለሚያደርግ” እና በአተገባበሩም ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትል ስለሆነ ነው” ተብሏል።
አወዛጋቢው ድንጋጌ ተካትቶ የነበረው፤ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ ነበር። እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከ12 ዓመት በፊት የወጣውን ህግ ያሻሻለው አዲሱ አዋጅ በፓርላማ የጸደቀው ሰኔ 10፤ 2017 ነበር።
በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራን በተመለከተ በአዋጁ የተካተተ ድንጋጌ፤ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችት ቀስቅሶ ሰንብቷል። ድንጋጌው “በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም” ይላል።
አዋጁ በጸደቀበት ዕለት የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ ያቀረበው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚቴ፤ ድንጋጌው እንዲካተት የተደረገው “ልዩ የምርመራ ስራን” “ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ነበር።

ዝርዝሩ

https://ethiopiainsider.com/2025/16248/