የአብይ አሕመድ የግል እስረኛ ሶስት አዳዲስ ክሶች ተመሰረቱባቸው

የፌደራሉ ዓቃቤ ሕግ በቀድሞው የሠላም ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት አዲስ ክሶች መመስረቱ ተሰማ ። ዓቃቤ ሕግ በታዬ ላይ አዲስ ከመሠረታቸው ክሶች መካከል አንዱ፣ የሕወሃት ኃይሎች በ2013 ዓ፣ም በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ዙሪያ ተከሳሹ ሃሰተኛ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ አሰራጭተዋል የሚል እንደሆነ የታዬ ጠበቃ አበራ ንጉሥ ተናግረዋል። ሌሎቹ ሁለት ክሶች ደሞ፣ ከጸረ ሠላም ኃይሎች ጋር በማበር መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ማሴር እና ድጋሚ ከመታሠራቸው በፊት “ሆርን ኮንቨርሴሽን” ለተሰኘ የበይነ መረብ ጣቢያ በሰጡት እና እስር ላይ ሳሉ በሦስት ክፍሎች በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው “የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል” የሚሉ መሆናቸውን ጠበቃቸው ነግረውናል። ፍርድ ቤቱ፣ በአዲሶቹ ክሶች ላይ የተከሳሹን መልስ ለመስማት ለኅዳር 23፣ 2018 ዓ፣ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን አስረድተዋል።