ኢትዮጵያ በተናጥል እና ባልተቀናጀ ሁኔታ ከፍተኛ ውሃ በመልቀቅ ችግር እየፈጠረች ትገኛለች ( ግብጽ )

የግብጽ የውሃና መስኖ ሚንስቴር፣ ኢትዮጵያ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተናጥል እና ባልተቀናጀ ሁኔታ ከፍተኛ ውሃ በመልቀቅ ችግር እየፈጠረች ትገኛለች በማለት ሰሞኑን አዲስ ክስ አቅርቧል። የግድቡ የውሃ አለቃቅ ተለዋዋጭነት በግድቡ ላይ ቴክኒካዊ እና ሳይንሳዊ አስተዳደር እንደሌለ ያሳያል በማለት የተቸው ሚንስቴሩ፣ ግብጽ በዚሁ ሳቢያ ከአስዋን ግድብ የቶሽካ ማስተንፈሻን ለመክፈት ተገዳለች ብሏል። ሚንስቴሩ “ያልተቀናጀ” እና “ሳይንሳዊ ያልሆነ” ያለው የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የውሃ አለቃቀቅ፣ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቦች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል በማለትም ወቅሷል። በተያዘው ኅዳር ወር ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከሕዳሴ ግድብ በቀን የተለቀቀው ውሃ 180 ሚሊዮን ሜትር ኪውብ መሆኑንና ይህም በዚህ ወቅት ቀደም ባሉት ዓመታት ይለቀቅ ከነበረው የውሃ መጠን በ80 በመቶ እንደሚበልጥ ሚንስቴሩ ጠቅሷል።