የእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ “ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ግጭት አፋፍ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ‘ፋኖ’ የተሰኘው ብሔርተኛ ሚሊሻ፣ ከዓለም በተቆረጡት የሰሜን-ምዕራብ ተራራማ አካባቢዎች ከመንግስት ጦር ጋር ከባድ ውጊያ ገጥሟል።’ በሚል የፎቶግራፍ ዘገባ፣ ሀገሪቱን እየበጣጠሰው ያለውን ውጥረት የሚያሳይ እይታን ይዞ ወጥቷል።
“የትግራይ ጦርነት ካበቃ ከሶስት ዓመታት በኋላ፣ ኢትዮጵያ በሰሜን-ምዕራብ ክፍሏ በተቀሰቀሰ ከባድ የትጥቅ አመጽ እየተናጠች ነው።” የሚለው ዘገባው፣ በአብዛኛው በቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የተዋቀረው “ፋኖ”፣ በአሁኑ ወቅት ሰፊውን የአማራ ክልል ገጠራማ አካባቢዎች (80% ገደማ) መቆጣጠሩን ሪፖርቱ ያሳያል።
ዘገባው እንዳመለከተው፣ የፌደራል ኃይሎች አመጹን ለማፈን በሚያደርጉት ጥረት “ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን” እየፈጸሙ ነው። ከእነዚህም መካከል አፈና፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ጾታዊ ጥቃቶች እና በሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ይገኙበታል።
“ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ነው” ያለው ዘገባው፣ በክልሉ ከሱዳን ጦርነት የሸሹ ስደተኞችን ጨምሮ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አፋጣኝ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል
በተለይም መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎችን “ለመበተን” መወሰኑ፣ በአማራ ተዋጊዎች ዘንድ እንደ ቀጥተኛ የጸጥታ ስጋት ተወስዷል። ዘገባው ይህንን “ጥልቅ የክህደት ስሜት” ሲል ይገልጸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባላትም የፋኖን ጦር በመቀላቀል፣ ወታደራዊ ልምዳቸውንና ትጥቃቸውን ይዘው የ20,000 ተዋጊዎችን ኃይል እንደፈጠሩ ተገልጿል።
ፋኖ እራሱን “የአማራ ህዝብ ተከላካይ” አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን፣ ግቡም ከክልሉ ሙሉ ቁጥጥር አንስቶ የዐቢይ አሕመድን መንግስት እስከመጣል ይደርሳል።
ሪፖርቱ እንዳነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ንጹሃን ዜጎች በግጭቱ መሃል ሆነው ከባድ ዋጋ እየከፈሉ ነው።
የ23 ዓመቷ ወ/ሮ ገቴ በየኖ፣ የ5 ዓመት ልጇን በእጇ ይዛ እርሻዋን ስታቋርጥ በመንግስት ኃይሎች ከተተኮሰ የሞርታር ጥይት ፍንጣሪ ልጇ “ተበጣጥሶ” ህይወቱ አልፏል። “በህይወት እንድኖር ምክንያት የሰጠችኝ በህይወት የተረፈችው ልጄ ብቻ ናት” ስትል ገቴ ለሪፖርቱ ተናግራለች።
በተመሳሳይ፣ ሌላ ነዋሪ ደግሞ የ83 ዓመት እናታቸው በፌደራል ድሮን በተመታ ቤታቸው ውስጥ እንደተገደሉ መስክረዋል።
እነዚህ ጥቃቶች በህዝቡ ዘንድ በማዕከላዊው መንግስት ላይ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሱ ሲሆን፣ ለፋኖ ህዝባዊ ድጋፍ እንዲጨምር አድርገዋል ተብሏል።
ጋዜጠኛ ቱቴንገስ በሰሜን ወሎ ላስታ አካባቢዎችን መጎብኘቱን ጠቅሷል። በአሁኑ ወቅት ክልሉ በፌደራል ኃይሎች (በዋና ከተሞች) እና በፋኖ (በገጠሮች) ተከፋፍሏል። በየቦታው በተቋቋሙ የፍተሻ ኬላዎች ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ህዝቡ እንዳይደርስ ታግቷል።
በሌላ በኩል፣ ሪፖርቱ ፋኖ እራሱ በትግራይ ጦርነት ወቅት በወልቃይት እና ራያ አካባቢዎች “የዘር ማጽዳት” እና ሌሎች ጥቃቶችን እንደፈጸመ ክሶች እንዳሉበት ጠቅሷል።
ምንም እንኳን ፋኖ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ቢኖረውም፣ ሪፖርቱ ሲያጠቃልል፣ እየጨመረ የመጣው የጸጥታ መደፍረስ እና የኢኮኖሚ ውድቀት፣ እንዲሁም በአንዳንድ የፋኖ ቡድኖች የሚፈጸመው “የገንዘብ ምዝበራ” ፣ ይህንን የህዝብ እምነት ቀስ በቀስ እየሸረሸረው መሆኑን አስረድቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አዲስ አበባ የትግራይ ኃይሎችን (ህወሓት) ከኤርትራ ጋር በመተባበር አዲስ ጦርነት ሊከፍቱ ነው ስትል ትከሳለች። በኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ዙሪያ የተፈጠረው የቃላት ጦርነትም፣ በትግራይ ጦርነት ከ600,000 በላይ ህዝብ ያለቀበትን የአፍሪካ ቀንድ፣ ለሌላ መጠነ ሰፊ ግጭት እያጋለጠው መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።